ግድቡ ኢትዮጵያዊያን በተደመረ ህብረት ከተንቀሳቀሱ አገራዊ ውጥንን ማሳካት እንደሚችሉ ህያው ምስክር ነው - ኢዜአ አማርኛ
ግድቡ ኢትዮጵያዊያን በተደመረ ህብረት ከተንቀሳቀሱ አገራዊ ውጥንን ማሳካት እንደሚችሉ ህያው ምስክር ነው
ድሬዳዋ፤ ነሐሴ 28/2017 (ኢዜአ)፦ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ኢትዮጵያዊያን በአንድነት ተደምረው ከተመሙ የትኛውንም አገራዊ ውጥን ከዳር ማድረስ እንደሚችሉ ያረጋገጡበት ህያው ምስክር ነው ሲሉ የድሬዳዋ አስተዳደር የህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሀብታሙ ዋቅጅራ ተናገሩ።
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የድሬዳዋ ማስተባበሪያ ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሀብታሙ ዋቅጅራ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ ግድቡ ኢትዮጵያዊያን እንደ ደመራ ተደምረው የይቻላልን መርህ ለትውልድ ያረጋገጡበት ህያው ፕሮጀክት ነው።
ከተባበርን የትኛውንም አገራዊ ጉዳይ በጋራ ማሳካት እንደምንችል ለትውልዱ ማረጋገጫ ይሆናል ብለዋል።
አቶ ሀብታሙ እንዳሉት ለግድቡ ዕውን መሆን የድሬዳዋ ነዋሪዎች፣ ተቋማትና ባለሃብቶች እንዲሁም በውጭ የሚኖሩ የድሬዳዋ ተወላጆችና ወዳጆች ከ108 ሚሊዮን ብር በላይ በቦንድ ግዥና በስጦት መልክ ማበርከታቸውን አንስተዋል ።
በተጠናቀቀው በጀት ዓመትም አምስት ሚሊዮን ብር የሚጠጋ የቦንድ ግዥ መፈፀማቸውን በማስታወስ።
ኢትዮጵያውያን በዕውቀት፣ በገንዘብ፣ በደምና በላባቸው ያጠናቀቁት የብልጽግና ጉዞ ማረጋገጫ ግድባችን ለምርቃት መብቃቱ ሁሉንም ያስደሰተና የኢትዮጵያን የታሪክ ቀያሪ ጎዳና የቀየሰ መሆኑን ነው የገለፁት።
እንደ አቶ ሀብታሙ ገለፃ የኢትዮጵያን የድህነት ታሪክ ስር ነቀል በሆነ መንገድ የሚለውጠውን ግድብ ዳር ለማድረስ የአገራችን አመራሮች ያሳዩት ዲፕሎማሲያዊ ጥበብና ብልሃት፣ ችግሮችን የተሻገሩበት ቁርጠኝነትና ትጋት ወሳኝ መሆኑን ነው።
የግድቡ ዕውን መሆን የኤሌክትሪክ ተደራሽነት፣ የቱሪዝም ፍሰትን ከማሳደግ ባሻገር ለማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ አብዮት እና የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት መሠረታዊ ሚናን ይጫወታል ብለዋል።
የህዳሴው ግድብ መጠናቀቁን ተከትሎ የድሬዳዋ ነዋሪዎች ለግድቡ ያደረጉትን የነቃ ተሳትፎ በቀጣይም በሌሎች አገራዊ ፕሮጀክቶች ላይ እንዲያጠናክሩ ለማስቻል በአዲሱ ዓመት መባቻ ህዝባዊ ንቅናቄ ለማካሄድ ዝግጅት መጠናቀቁን አቶ ሀብታሙ አውስተዋል።
ከመጪው መስከረም 2 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ ለአንድ ሳምንት በሚካሄዱት ሁነቶች ህዝቡ ለግድቡ እና ለሌሎች ልማቶች ያለውን ድጋፍና ተሳትፎ የሚያረጋግጥበት ይሆናል ብለዋል።