ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የአይቻልምን መንፈስ የሰበረ ፕሮጀክት ነው - ኢዜአ አማርኛ
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የአይቻልምን መንፈስ የሰበረ ፕሮጀክት ነው
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 28/2017 (ኢዜአ)፦ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የአይቻልምን መንፈስ የሰበረ እና መተባበር ጎልቶ የታየበት ታላቅ ፕሮጀክት መሆኑን ኢዜአ ያነጋገራቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ተናገሩ።
የጠምባሮ ብሔረሰብ የባህል፣ ቋንቋና ታሪክ ሲምፖዚም "የባህልና የቋንቋ ዕድገት ለህዝቦች አንድነትና ለዘላቂ ልማት" በሚል መሪ ሃሳብ በአዲስ አበባ ተካሂዷል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ መጠናቀቅን አስመልክቶ ኢዜአ ያነጋገራቸው የሲምፖዚየሙ ተሳታፊዎች ፤ ታላቁ የህዳሴ ግድብ አንድነታችንን ያረጋገጥንበት ሀገራዊ ፕሮጀክት ነው ብለዋል፡፡
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በርካታ ውጣ ውረዶችንና ፈተናዎችን አልፎ ለምረቃው ዋዜማ በመድረሱ መደሰታቸውን ተናግረዋል፡፡
ግድቡ ከተጀመረ ጀምሮ በገንዘብና በጉልበት እንዲሁም ቦንድ በመግዛት ድጋፍ ሲያደርጉ መቆየታቸውን ገልጸዋል፡፡
አቶ ሙላቱ ሽሙሬ የኢትዮጵያውያን ኩራት የሆነው የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከተጀመረ አንስቶ የበኩላቸውን ድጋፍ ማድረጋቸውን አስታውሰዋል፡፡
ታላቁ የህዳሴ ግድብ መጠናቀቅ የአይቻልምን መንፈስ የሰበረና በጋራ እንድንቆም ያደረገ ነው በማለት፤ ግድቡ እውን ሆኖ በማየታቸው መደሰታቸውን ተናግረዋል፡፡
ሌላኛው አስተያየት ሰጭ አቶ ሙሉጌታ በላቸው በበኩላቸው፤ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ እውን መሆን በቀጣይ ሌሎች ታላላቅ የልማት ስራዎችን ማሳካት እንደሚቻል የታየበት መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከተበሰረበት ጊዜ ጀምሮ ቦንድ በመግዛት ድጋፍ ሲያደርጉ መቆየታቸውን በመግለጽ፤ የግድቡ መጠናቀቅ በተለይ የእናቶችን ድካም በእጅጉ የሚያቃልል ነው ያሉት ደግሞ ሌላኛዋ አስተያየት ሰጭ ወይዘሮ በላይነሽ ሮሞ ናቸው።
አቶ ሃይለሚካኤል አሸንጎ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ እውን መሆኑ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ አንድ ደረጃ ከፍ እንደሚያደርገው ተናግረዋል፡፡
በተለይም ግብርናውንና ኢንዱስትሪውን በማዘመን ኢትዮጵያን ከፍ ወዳለ ደረጃ ያሸጋግራታል ብለዋል፡፡