ቀጥታ ስርጭት

ለኢትዮጵያ የማንሰራራትና የከፍታ ጉዞ የተደመረ ጥረታችን ይቀጥላል- ርእሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ

ሀዋሳ ፤ ነሐሴ 28/2017 (ኢዜአ)፦  የክልሉን ዕምቅ ሃብት በማልማት ለኢትዮጵያ የማንሰራራትና የከፍታ ጉዞ የተደመረ አቅማችን እና ጥረታችን ይቀጥላል ሲሉ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርእሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ ገለጹ።

በክልሉ ሁለንተናዊ የልማት እንቅስቃሴና በተለያዩ መስኮች የተመዘገቡ ስኬቶችና ቀጣይ አቅጣጫዎችን በተመለከተ ኢዜአ ከርእሰ መስተዳድሩ ጋር ቆይታ አድርጓል።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል እምቅ ሃብትና ሰፊ የመልማት አቅም እንዳለው ያነሱት ርእሰ መስተዳድሩ በሚፈለገው ልክ ሳይለማና ጥቅም ላይ ሳይውል መቆየቱን አንስተዋል።

በመሆኑም ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ በክልሉ ያለውን እምቅ የተፈጥሮ ሃብትና የቱሪዝም መስህብ እንዲሁም የግብርና ልማት ምርታማነት የማሳደግ ስራ በስፋት እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል።

በኢንዱስትሪ፣ ማኑፋክቸሪንግ፣ ማዕድንና የቱሪዝም ዘርፍ ያለውን ዕምቅ ሃብት በማልማት ጥቅም ላይ የማዋል ስራ ትኩረት የተሰጠው መሆኑን አንስተዋል።

በቀጣይም የክልሉን ዕምቅ ሃብት በማልማት ለኢትዮጵያ የማንሰራራት ጅማሮና የከፍታ ጉዞ የተደመረ አቅማችንና ጥረታችን ተጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉ አረጋግጠዋል።

በማህበራዊ ዘርፍ የትምህርት ጥራትና ተደራሽነትን በማስፋት እንዲሁም በጤናው ዘርፍ የተከናወኑ ተግባራትም መሰረታዊ ለውጥና የላቀ ውጤት የተመዘገበባቸው መሆኑን አንስተዋል።

በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ሁሉንም አሳታፊ ያደረገ የዴሞክራሲ ስርአት ግንባታ ሂደት ተጀምሯል ያሉት ርእሰ መስተዳድሩ የጋራ ትርክትና ህብረ ብሄራዊ አንድነትን የማጽናት ስራ ይቀጥላል ብለዋል።

በክልሉ ለሚከናወኑ የልማት ስራዎች መሳካት የገቢ አቅምን ማሳደግ ወሳኝ በመሆኑ በዚህ ረገድም ጥረቶች እየተደረጉ መሆኑን ርእሰ መስተዳድሩ አንስተዋል።

በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 20 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር ገቢ መሰብሰቡን አስታውሰው በተያዘው በጀት አመት ከ31 ቢሊየን ብር በላይ ለማድረስ ግብ ተይዞ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡

በክልሉ በሁሉም ረገድ የተጀመሩ የልማት ስራዎችን በውጤታማነት ለማስቀጠል የተቀናጀ ጥረት የሚደረግ መሆኑን አንስተው በዚህ ረገድ በየደረጃው ያለው አመራር ስራና ሃላፊነቱን በብቃት መወጣት እንዳለበት አስገንዝበዋል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም