በጋምቤላ ክልል የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ መጠናቀቅን በማስመልከት የተለያዩ ሁነቶች እየተካሄዱ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በጋምቤላ ክልል የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ መጠናቀቅን በማስመልከት የተለያዩ ሁነቶች እየተካሄዱ ነው
ጋምቤላ፤ ነሐሴ 28/2017 (ኢዜአ)፦ በጋምቤላ ክልል ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ መጠናቀቅን በማስመልከት ልዩ ልዩ ሁነቶች እየተካሄዱ መሆኑን የክልሉ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት አስታወቀ።
’’ግድባችን የመቻል ማሳያ፤ የማንሰራራት ጅማሮ ምልክት’’ በሚል መሪ ሐሳብ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮችና ወጣቶች የተሳተፉበት የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ዛሬ በጋምቤላ ከተማ ተካሄዷል።
የጽህፈት ቤት ኃላፊ ኮማንደር ጋድቤል ቦል በመርሃ ግብሩ ላይ እንደገለጹት በክልሉ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ፍፃሜን በማስመልከት የተለያዩ ሁነቶች እየተካሄዱ ነው።
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ተጀምሮ ከፍፃሜ እስኪደርስ የክልሉ ህዝብ በቦንድ ግዥና በሌሎች ተሳትፎዎች ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን አስታውሰዋል።
በመሆኑም የህዳሴ ግድብ ግንባታ ከፍፃሜ መድረሱን በማስመልከት እስከ መስከረም 10 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ የሚዘልቅ የተለያዩ ሁነቶች መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።
ከተሰናዱት ሁነቶች መካከል የአካባቢ ጽዳትና እንክብካቤ፣ የስፖርት ውድድሮች፣ የድጋፍ ሰልፎችና ሌሎች የልማት ሥራዎች እንደሚገኙበት የጽህፈት ቤት ኃላፊው ተናግረዋል።
የክልሉ ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር ጃይኮብ ኒያል በበኩላቸው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከፍፃሜ መድረሱን ተከትሎ ከክልል እስከ ወረዳ የዘለቀ የስፖርት እንቅስቃሴና የውድድር መርሃ ግብሮች መካሄድ ጀምረዋል ብለዋል።
በመርሃ ግብሩ ከሚካሄዱት የስፖርት ውድድሮች መካከል ቅርጫት ኳስ፣ ሩጫ፣ የእግር ኳስና ሌሎችም እንደሚገኙበት ኮሚሽነር ጃይኮብ ገልጸዋል።
ከሰሞኑ የዚሁ ሁነት አካል የሆነው እና የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ዓለሚቱ ኡሞድን ጨምሮ የክልሉ ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች የተገኙበት የጋምቤላ ስታዲየም አካባቢ የጽዳት ዘመቻ መካሄዱ ይታወሳል።