ቀጥታ፡

ታላቁ የህዳሴ ግድብ በጋራ ጥረትና ትብብር እውን የሆነ የትውልዱ አኩሪ ታሪክ ነው

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 27/2017(ኢዜአ)፦ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በጋራ ጥረትና ትብብር እውን የሆነ የትውልዱ አኩሪ ታሪክ ነው ሲሉ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ ረዳት ፕሮፌሰር ነብዩ ባዬ ገለፁ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ሀገርን በጥበብ በሚል የሚያዘጋጀው ወርሃዊ የስነ-ፅሁፍ መርሃ-ግብር "ህዳሴን በጥበብ" በሚል መሪ ሀሳብ ተካሂዷል።


 

በመርሃ-ግብሩ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ ረዳት ፕሮፌሰር ነብዩ ባዬን ጨምሮ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አረጋዊ በርሄ (ዶ/ር)፤ አንጋፋው ደራሲ ጸሃፊ ተውኔትና ተዋናይ ጌትነት እንየው የጥበብ ባለሙያዎች፣ ገጣሚያንና የኢዜአ የአመራር አባላትና ሰራተኞች ታድመዋል።

የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ ረዳት ፕሮፌሰር ነብዩ ባዬ በወቅቱ፤ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለኢትዮጵያውያን እጅግ አስገራሚና አስደማሚ ልዩ ታሪካችን ነው ሲሉ ገልጸዋል።

ደራስያንና ገጣሚያን ይህን ድንቅ ግድብ ለመግለፅ በቃላት ይጠበቡበታል ብለዋል።

ግድቡ ከግዙፍነቱ በላይ በኢትዮጵያውያን የጋራ ጥረትና ትብብር እውን የሆነ የትውልዱ አኩሪ ታሪክ መሆኑንም ነው የተናገሩት።

ታላቁ የህዳሴ ግድብ ለኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ልዮ ታሪክ መሆኑን አንስተው፤ የግድቡ መጠናቀቅ ሌሎች ፕሮጀክቶችን ለመጀመር መነሳሳት ይፈጥራል ብለው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም