አረንጓዴ አሻራ- የአፍሪካ ሀገር በቀል የአየር ንብረት ለውጥ መፍትሄ ተምሳሌት - ኢዜአ አማርኛ
አረንጓዴ አሻራ- የአፍሪካ ሀገር በቀል የአየር ንብረት ለውጥ መፍትሄ ተምሳሌት
አፍሪካ ለአየር ንብረት ለውጥ ድርሻዋ ከዚህ ግባ የማይባል ሆኖ ሳለ የተጽእኖው ተጎጂ እየሆነች ትገኛለች።
የሙቀት መጨመር፣ የተራዘመ ድርቅ እና ኢ-ተገማች የሆነ የዝናብ ሁኔታ አህጉሪቷ እየተጋፈጠቻቸው ካሉ ችግሮች መካከል ተጠቃሽ ናቸው።
ይሁንና አፍሪካ በነዚህ ፈተናዎች ውስጥ ሁሉ ሆና የራሷን ሀገር በቀል የአየር ንብረት ለውጥ መፍትሄዎች ገቢራዊ እያደረገች ነው።
መፍትሄዎቹ የአፍሪካ የካበቱ እውቀቶች እና ብልሃቶችን ከዘመናዊ የኢኖሼሽን ስራ አጣምረው የያዙ ናቸው።
ከመፍትሄዎች መካከልም አንዱ የኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ነው።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ሀሳብ አመንጪነት በ2011 ዓ.ም በተጀመረው አረንጓዴ አሻራ እስከ አሁን ከ47 ቢሊዮን በላይ ችግኞች መተከላቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ።
አረንጓዴ አሻራ በአፍሪካ ለአየር ንብረት ለውጥ ከተሰጡ ሀገር በቀል ምላሾች መካከል በዋናነት የሚጠቀስ ነው።ኢኒሼቲቩ ሀገር በቀል እውቀት፣ የጋራ ተግባር እና መጠነ ሰፊ ማህበረሰብ ተሳትፎን በማቀናጀት ስኬታማ የሆነ ለዓለም የሚደርስ የአየር ንብረት ለውጥ መፍትሄ ማምጣት እንደሚቻል በተግባር የሚያሳይ ነው።
አረንጓዴ አሻራ ከአካባቢ ጥበቃ ትሩፋቶቹ፣ የተራቆተ መሬትን ወደ ነበረበት ከመመለስ፣ የውሃ ሀብት አስተዳደርን በመጨመር እና የምግብ ሉዓላዊነት ከማረጋገጥ አንጻር ካለው ፋይዳ ባሻገር አፍሪካ ለአየር ንብረት ለውጥ ተግዳሮት ከውጭ መፍትሄ እስኪመጣ ከመጠበቅ በራሷ አቅም መፍትሄን ማመንጨት እንደምትችል የሚያሳይ ነው።
በአየር ንብረት ለውጥ ተጎጂ የሆኑ ማህበረሰቦች ለጉዳዩ በጋራ በመቆም እና የመፍትሄው አካል በመሆን የአካባቢ ጥበቃ ዘብ መሆናቸውንም ለማየት ተችሏል።
አዛውንት፣ ወጣት፣ ሴት፣ ወንድ፣ የማህበረሰብ መሪ፣ የጤና ባለሙያ፣ አመራር፣ ተማሪ እና ባለሀብትን ጨምሮ ሁሉም አሻራውን ያሳረፈበት ታላቅ ሀገራዊ ፕሮጀት ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በቅርቡ አረንጓዴ አሻራ ኢትዮጵያ ትላልቅ ነገር አስገባ፣ትላልቅ ነገር ተልማ፣ ትላልቅ ነገር አቅዳ እና ህዝቦቿን አስተባብራ ማሳካት እንደምትችል ለሌሎቹ ማሳያ መሆኑን የተናገሩበት ሀሳብ የህዝቡን የነቃ ተሳትፎ የሚያሳይ ነው።
በተለይም በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎች በነቂስ ወጥተው መሳተፋቸው የሀገርን የጋራ ራዕይ ለማሳካት ያላቸውን ፍላጎት እና ቁርጠኝነት የሚያሳይ እንደሆነም አመልክተዋል። አረንጓዴ አሻራ የኢትዮጵያ ትልቅ የታሪክ አሻራ አካል ነው ሲሉም ገልጸዋል።
በሌላ በኩል ኢኒሼቲቩ ኢትዮጵያ እየገነባች ላለው የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ ያለው ድርሻ ከፍተኛ ነው።
የደን ሽፋን መጨመር፣ የምግብ ምርታማነት ማደግ፣ የስራ እድል ፈጠራ፣ የካርቦን ልቀት መቀነስ፣ የብዝሃ ህይወቶች ዳግም እያገገሙ መምጣት እና ሌሎች ተጓዳኝ ስኬቶች አረንጓዴ አሻራ ከአይበገሬነት አልፎ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ እያስገኘ እንደሚገኝ ማረጋገጫ ናቸው።
ኢትዮጵያ ለአረንጓዴ አሻራ በየጊዜው የሚዋዥቀውንና የሌሎች ቸርነት ላይ የተመሰረተውን የውጭ እርዳታ ሳትጠብቅ ሀገር በቀል የፋይናንስ አቅም መጠቀሟ ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ምሳሌ ሆኗል።
በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር አማካኝነት ኢትዮጵያ ለጎረቤት ሀገራት ችግኞችን በመላክ እና እንዲሳተፉ በማድረግ ቀጠናዊ አጋርነቷንም በተግባር ገልጣለች።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የዘንድሮው አረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ማስጀመሪያ ላይ ለተገኙት የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ካሺም ሼቲማ የአራት ሺህ ችግኞች ስጦታ ማበርከታቸው የሚታወስ ሲሆን በምላሹም ናይጄሪያ ለኢትዮጵያ 2 ሺህ የካሽው ችግኝ እና 100 ሺህ ዘር በሥጦታ አበርክታለች። ይህ አረንጓዴ አሻራ የፓን አፍሪካን የአጋርነት መንፈስ አዲስ መገለጫ እና ጉዳዩ የአፍሪካ አጀንዳ እየሆነ መምጣቱን አመላካች ሲሆን አፍሪካውያን በአካባቢ ጥበቃ ዘላቂ ትብብር መፍጠር እንዳለባቸውም የሚያስገነዝብ ነው።
አረንጓዴ አሻራ ከአፍሪካ ህብረት ትልቁ ማዕቀፍ አጀንዳ 2063 ጋር የሚጎዳኙ ጉዳዮች አሉት። አጀንዳ 2063 የበለጸገች እና አረንጓዴ አፍሪካን እውን ሆኖ የማየት ህልምን ያነገበ ነው። በደን መልሶ ልማት እና ዘላቂ ግብርና ስራ የመሪነት ሚና እየተወጣች የምትገኘው ኢትዮጵያ ከአጀንዳ 2063 ቁልፍ ግቦች መካከል ለስነ ምህዳር መልሶ ማገገም፣ ሁሉን አቀፍ ልማት እና ቀጣናዊ ትብብር ቀጥተኛ አስተዋጽኦ እያደረገች ትገኛለች።
የአረንጓዴው አብዮት በአዲስ አበባ ከጳጉሜን 3 እስከ 5 ቀን 2017 ዓ.ም ከሚካሄደው ሁለተኛ የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባኤ ጋር የተጋመደ ነው።ከጉባኤው አጀንዳዎች መካከል የአፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ መፍትሄዎች የተሞክሮ ልውውጥ አንዱ ሲሆን ኢትዮጵያም የአረንጓዴ አሻራ ስኬታማ ተሞክሮዋን በስፋት ታጋራለች።
ከአፍሪካ አልፎ በዓለም እውቅናው እየናኘ የመጣው አረንጓዴ አሻራ የኢትዮጵያን የአየር ንብረት ለውጥ በመከላከል በኩል ያላትን የመሪነት ሚና የሚያሳይ ነው።
ኢኒሼቲቩ ከአየር ንብረት ግቦች ባሻገር ከኢኮኖሚ ጋር የተሰናሰነ ሲሆን ይህም አረንጓዴ እድገት የስራ እድልን በመፍጠር፣ ፍትሃዊነትን በማረጋገጥ እና እድሎችን በማስፋት ረገድ ወሳኝ ሚና አለው።
እንደ አረንጓዴ አሻራ ያሉ ከውስጥ የሚነጩ መፍትሄዎች አፍሪካ ለራሷ ጉዳይ ራሷ መፍትሄ ሰጪ የመሆን አቅሟን የሚያሳድግ፣ በዓለም መድረክ ያላትን ተሰሚነት የሚያሳድግ እና መጻኢ ጊዜዋን ብሩህ የሚያደርግ ነው።