ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ  ኃይል በደሴ ከተማ የአቅመ ደካሞች የቤት ግንባታ እና እድሳት ስራ አስጀመረ

‎ደሴ ፤ ነሐሴ 27/2017 (ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ  ኃይል በደሴ ከተማ የአቅመ ደካሞችን የቤት ግንባታ እና እድሳት ስራ አስጀመረ። 

በመርሃ ግብር ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ  ኃይል የትራንሚሽን ቢዝነስ ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኢንጂነር አንዱዓለም ሲዓ፤ ተቋሙ ከመደበኛ ተግባሩ በተጨማሪ የማህበራዊ አገልግሎት ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።


 

በዚህም መሰረት በዛሬው እለት የአቅመ ደካማ ቤቶችን ግንባታና እድሳት በማስጀመር ለተማሪዎች ደግሞ የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ አድርገናል ብለዋል።

የቤቶቹን ግንባታ በጥራትና በፍጥነት በማጠናቀቅ ለማስረከብ የሚሰራ መሆኑን ገልጸው ተቋማቸው የኃይል አቅርቦትና ተደራሽነትን ከማስፋትም ባለፈ ማህበራዊ አገልግሎቱን አጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን አረጋግጠዋል።


 

የደሴ ከተማ አስተዳደርን በመወከል የተገኙት ኮማንደር ሰይድ አሊ፤  የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ  ኃይል ከመደበኛ ተግባሩ ባለፈ በማህበራዊ አገልግሎቱ እያደረገ ላለው አስተዋጽኦ አመስግነዋል።


 

በከተማዋ በተቋሙ የተጀመረው የአቅመ ደካሞችን ቤት የመገንባት ስራ በጥራትና በፍጥነት እንዲጠናቀቅ ከተማ አስተዳደሩ ተገቢውን ክትትልና ድጋፍ የሚያደርግ መሆኑን ተናግረዋል።

በእለቱ የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ የተደረገላቸው ተማሪዎችና ወላጆቻቸው እንዲሁም የቤት ግንባታና እድሳት የሚደረግላቸው ዜጎች ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ  ኃይል ምስጋና አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም