ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የአፍሪካ ትስስር በማጠናከር ቁልፍ ሚና እየተወጣ ነው- መሐሙድ አሊ ዩሱፍ  

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 27/2017 (ኢዜአ)፦  የኢትዮጵያ አየር መንገድ የአፍሪካ ትስስር የበለጠ እንዲያድግ ጉልህ አስተዋጽኦ እያደረገ እንደሚገኝ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር መሐሙድ አሊ ዩሱፍ ገለጹ። 

የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር መሐሙድ አሊ ዩሱፍ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰውን ዛሬ በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።


 

የኮሚሽኑ ሊቀ መንበር የኢትዮጵያ አየር መንገድ የአፍሪካ አየር መንገድ መሆኑን ገልጸው የአፍሪካ ህብረት ስራዎች እና የአጀንዳ 2063 ራዕይ እንዲሳካ እየተወጣ ያለውን ሚና አድንቀዋል።

አየር መንገዱ በአፍሪካ ትስስርን፣ ንግድ እና እንቅሰቃሴን በማሳለጥ ለአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጣና እና ለአፍሪካ ነጠላ የአየር ትራንስፖርት ገበያ ቀጥተኛ ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝ አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው የአፍሪካ ህብረት እና አየር መንገዱ ለረጅም ጊዜ የዘለቀ ወዳጅነት እንዳላቸው ገልጸዋል።

አየር መንገዱ ከአየር ትራንስፖርት ባለፈ የአፍሪካን የትስስር አጀንዳ ውጤታማ እንዲሆን ከህብረቱ በቅርበት በመስራት የፓን አፍሪካ ተቋም ሆኖ እየሰራ እንደሚገኝ አመልክተዋል።

ዋና ስራ አስፈጻሚው አየር መንገዱ አፍሪካን ከተቀረው ዓለም ጋር በማስተሳሰር፣ የአፍሪካን ወጣቶች በአቪዬሽን ዘርፍ በማሰልጠን፣ ሌሎች በአፍሪካ የሚገኙ ብሄራዊ አየር መንገዶችን በመደገፍ እና የሰላም  ፈንድን ጨምሮ ለአፍሪካ ህብረት የተለያዩ ኢኒሼቲቮች አስተዋጽኦ በማድረግ የድርሻውን እየተወጣ እንደሚገኝም ነው ያብራሩት።

ሁለቱ ወገኖች በውይይታቸው የአፍሪካ ህብረት እና የኢትዮጵያ አየር መንገድ አጋርነት ለማጠናከር ከስምምነት ላይ ደርሰዋል።

አየር መንገዱ የአፍሪካን ትስስር እና ትብብር ከማጠናከር ጎን ለጎን በአጀንዳ 2063 ማዕቀፍ ስር የተቀመጡ የአፍሪካ ህብረትን ሁሉን አቀፍ ራይዕ ለማሳካት እንደሚሰራ መግለጹን ኢዜአ ከአፍሪካ ህብረት ያገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም