የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ምርቃትን አስመልክቶ የተለያዩ መርሃ ግብሮች ይካሄዳሉ - ኢዜአ አማርኛ
የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ምርቃትን አስመልክቶ የተለያዩ መርሃ ግብሮች ይካሄዳሉ
አዲስ አበባ፤ነሐሴ 27/2017(ኢዜአ)፦የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ምርቃትን አስመልክቶ ከሁለት ሺህ በላይ ሰዎች የሚሳተፉበት ህዝባዊ መድረክና የስዕል አውደ ርዕይ እንደሚካሄድ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አረጋዊ በርሄ (ዶ/ር) ገለፁ።
ጽህፈት ቤቱ ከኢትዮ-ቴሌኮም ጋር በመተባበር ዜጎች መልካም ምኞታቸውን የሚገልጹበት "የትውልድ አሻራ ዲጂታል የብስራት መልዕክትና ገቢ ማስገኛ ፕሮጀክት" በሚል ስያሜ መልዕክት ማስተላለፍ የሚያስችል ዕድል ፈጥሯል።
የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አረጋዊ በርሄ (ዶ/ር)፤ ታላቁ የሕዳሴ ግድብ የወል ትርክታችንና ላባችንን ቀለም፣ ክንዳችንን ደግሞ ብዕር አድርገን የፃፍነው መፅሀፍ ነው ብለዋል።
ታላቁ ሕዳሴ ግድብ ታሪክ የሰነደ፣ ከተባበርን የዕድገት ማማ ላይ መውጣት እንደምንችል ያሳየ መሆኑን ተናግረዋል።
ታላቁ ሕዳሴ ግድብ ለሌሎች ግድቦች መነሻ የሚሆን የቁጠባ ባህልን የሚያሳድግ ፣የአንችልምን መንፈስ የሰበረ የዚህ ትውልድ አዲስ ትርክት ሆኖ የተመዘገበ ዳግማዊ አድዋ ነው ብለዋል።
ህብረተሰቡ ለሕዳሴ ግድብ ግንባታ የበኩሉን ሲወጣ መቆየቱን ጠቁመው፤ በኢትዮ ቴሌኮም በ"8100 A" ላይ በመላክ በተከታታይ ለሶስት ዙር የድጋፍ ማሰባሰብ ስራ መሰራቱን ገልጸዋል።
የግድቡን መመረቅ አስመልክቶ ከሁለት ሺህ በላይ ሰዎች የሚሳተፉበት ህዝባዊ መድረክና የስዕል አውደ ርዕይ መርሃ ግብር እንደሚካሄድ ተናግረዋል።
ከዛሬ ጀምሮ ህብረተሰቡ 8120ን በመጠቀም ደስታውንና ስሜቱን ማጋራት ይችላል ነው ያሉት።
የኢትዮ ቴሌኮም ቺፍ ኮሙዩኒኬሽን ኦፊሰር መሳይ ውብሸት በበኩላቸው፤ ኢትዮ-ቴሌኮም ለታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ በ8100 ገቢ ከማሰባሰብ ባለፈ በቦንድ ግዥና ድጋፍ የበኩሉን ሲወጣ መቆየቱን ተናግረዋል።
ተቋሙ አሁን ላይ በተጀመረውና ለ33 ቀናት በሚቆየው የድል ብስራት ማብሰሪያና ሌሎች ተግባሮችም በጋራ ለመስራት ዝግጁ መሆኑን ገልፀዋል።
የአጭር መልዕክት ማስተላለፊያ ኮዱ ከዛሬ ነሃሴ 27 ቀን 2017 እስከ መስከረም 30 ቀን 2018 ድረስ ባሉት ጊዜያት ህብረተሰቡ ለታላቁ ሕዳሴ ግድብ እውን መሆን ሲያደርግ የነበረውን ድጋፍ በተመለከተ በአጭር መልዕክት ሃሳቡን በመግለፅ አሻራውን ለታሪክ መዘክርነት ማስቀመጥ የሚችልበት ነው።
በአጭር መልዕክት ማስተላለፊያ ኮዱ 1 ቁጥር መላክ አምስት ብር ድጋፍና በህብረት ችለናል የሚል መልዕክት ያለው ሲሆን፤ 2 ቁጥር ደግሞ የ10 ብር ድጋፍና ታላቁ ሕዳሴ ግድብ የብልፅግና አሻራ የሚል መልዕክት ያለው መሆኑ ተገልጿል።
3 ቁጥር የ15 ብር ድጋፍና ግድባችን የአሸናፊነት ድል አክሊል እንዲሁም 4 ቁጥር የ100 ብር ድጋፍና ግድባችን የአባይ ዘመን ትውልድ የተጋድሎ ሰንደቅ የሚል መልዕክት ያላቸው መሆኑ ተጠቁሟል።
በተጨማሪም ህብረተሰቡ የራሱን መልዕክት ሲልክ 20 ብር ድጋፍ እንደሚያደርግም ነው የተገለፀው።
ኢትዮጵያዊያን በታላቁ ሕዳሴ ግድብ ዙሪያ ያላቸውን ስሜት፣ ሃሳብና መልዕክት ለታሪክ ከትቦ ማስቀመጥ የህዝባዊ ተሳትፎ አካል በመሆኑ ሁሉም ኢትዮጵያዊ መልዕክቱን በመግለፅ ለትውልድ የሚያስተላልፍበት ፕሮጀክት ማስፈለጉ ተገልጿል።