ቀጥታ፡

የኢንዱስትሪ ፖሊሲ በአዲስ መልክ መዘጋጀቱ ዘርፉ ተመራጭና ተወዳዳሪ እንዲሆን ጉልህ አስተዋጽኦ አበርክቷል

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 27/2017(ኢዜአ)፦ የኢንዱስትሪ ፖሊሲ በአዲስ መልክ መዘጋጀቱ የኢኮኖሚ እድገትን ለማረጋገጥ አስቻይ ሁኔታ ከመፍጠሩ ባለፈ ዘርፉ ተመራጭና ተወዳዳሪ እንዲሆን ጉልህ አስተዋጽኦ ማበርከቱን የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ ታረቀኝ ቡሉልታ ገለጹ።

የሀገሪቱን እድገት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር በትኩረት እየተሰራባቸው ካሉ ዘርፎች መካከል ኢንዱስትሪ አንዱ ነው።

የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ ታረቀኝ ቡሉልታ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለጹት እንደ አገር ሁለንተናዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ በተከናወኑ ተግባራት ተጨባጭ ውጤት ተመዝግቧል።

በተለይም የኢንዱስትሪ ዘርፍ ከአምስቱ የኢኮኖሚ የልማት ምሰሶዎች ውስጥ መካተቱ አቅሞችንና ሃብቶችን አሟጦ ለመጠቀም እድል መፍጠሩን ጠቅሰዋል።

በዚህም ዘርፉ በኢኮኖሚው ውስጥ ያለው ተሳትፎ እንዲጨምርና ቀጣይነት ያለው እድገት እንዲያረጋግጥ ጉልህ አስተዋጽኦ አበርክቷል።

ቀደም ሲል ጥቅም ላይ የነበረው የኢንዱስትሪ ፖሊሲ ዓመታትን ያስቆጠረ፣ ወቅታዊና ዓለም አቀፋዊ ሁኔታን ያገናዘብ ባለመሆኑ ማሻሻያ እንዲደረግበት መወሰኑ ከተከናወኑ ተግባራት መካከል አንዱና ዋነኛው ነው ብለዋል፡፡

የዘርፉን አሰራር ማዘመን የሚያስችልና 18 ስትራጂዎችን ያካተተ የአምራች ኢንዱስትሪ ፖሊሲ በአዲስ መልክ በማዘጋጀት ተግባራዊ መደረጉን ሚኒስትር ዴኤታው አብራርተዋል።

ፖሊሲው ምርታማነትን ለመጨመርና የኢኮኖሚ እድገትን ለማረጋገጥ አስቻይ ሁኔታ ከመፍጠሩ ባለፈ ዘርፉ ተመራጭ፣ ሳቢና ተወዳዳሪ እንዲሆን ጉልህ አስተዋጽኦ ማበርከቱን አንስተዋል።

በዋናነት የኢትዮጵያ ታምርት አገራዊ ንቅናቄ የዘርፉን ምርታማነት ለመጨመርና የአምራች ኢንዱስትሪውን ችግር ለመፍታት የማይተካ ሚና እያበረከተ መሆኑን አንስተዋል።

በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ 875 ኢንዱስትሪዎች ወደ ስራ መግባታቸውን የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታው ንቅናቄው ለአምራች ኢንዱስትሪው ትልቅ እድል ይዞ መምጣቱንም አስታውቀዋል።

በተጨማሪም የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉን ከማስፋፋት አኳያ በቂ የመሰረተ ልማት አቅርቦት ሌላኛው የትኩረት አቅጣጫ መሆኑን ተናግረዋል።

በተለይም የሎጂስቲክስ ስርዓቱን ማዘመን የሚያስችሉ የመንገድ፣ የባቡርና የሃይል አቅርቦት ተደራሽነትን ለማረጋገጥ አመርቂ ተግባራት መከናወናቸውን አክለዋል።

በአጠቃላይ በኢንዱስትሪ ዘርፉ የተካሔዱ የአሰራር ማሻሻያዎች በዘርፉ የሚመዘገበው እድገት ዘላቂና ቀጣይነት እንዲኖረው አስችሏል ብለዋል።

ለአብነትም በ2016 በጀት ዓመት 10 ነጥብ 1 እድገት መመዝገቡን ጠቁመው በ2017 በጀት ዓመት ወደ 10 ነጥብ 4 ከፍ ማድረግ ተችሏል ነው ያሉት።

የዘርፉን ምርታማነት ለማሳደግ በልዩ ትኩረት በተከናወኑ ተግባራት ምጣኔውን ከ44 በመቶ ወደ 65 በመቶ ማሳደግ መቻሉን አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም