ቀጥታ፡

በዞኑ በለውጡ ዓመታት የተመዘገቡ የመሰረተ ልማት ስኬቶች የበለጠ ለስራ አነሳስቶናል-- የነገሌ ቦረና ከተማ ነዋሪዎች

ነገሌ ቦረና ፤ ነሃሴ 27/2017 (ኢዜአ):-በምስራቅ ቦረና ዞን በለውጡ ዓመታት የተመዘገቡ የመሰረተ ልማት ስኬቶች የበለጠ ለስራ እንዳነሳሳቸው የነገሌ ቦረና ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ፡፡ 

ነዋሪዎቹ በወቅታዊ አገራዊና አካባቢያዊ የሰላምና የልማት ጉዳዮች ዙሪያ በነገሌ ቦረና ከተማ መክረዋል፡፡ 

በውይይት መድረኩ ላይ ከተገኙት ነዋሪዎች መካከል አቶ አክሊሉ ለማ መድረኩ ባለፉት ዓመታት በተከናወኑ የልማት ስራዎች ላይ በመወያየት ጥንካሬዎችና ክፍተቶችን ለይተን ለመንግስት ጥቆማ የምናሳውቅበት ነው ብለዋል፡፡

በአዲሱ የቀበሌ አደረጃጀት ፍትሃዊ አገልግሎት አሰጣጥን ተደራሽ ለማድረግ የተጀመረው ስራ የሚደገፍና የሚበረታታ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡

የተገኙ ድሎችና ስኬቶችን ከማድነቅ ባለፈ ሁላችንም በከተማዋ እየተከናወኑ ባሉ የልማት ስራዎች ላይ በበጎ ፈቃደኝነት መሳተፍ ይገባናል ብለዋል።

በለውጡ ዓመታት የተከናወኑ የመሰረተ ልማት ግንባታዎች በቁጭትና በሞራል ለበለጠ ስራ የሚያነሳሱ ናቸው ያሉት ደግሞ ሌላኛዋ የውይይቱ ተሳታፊ ወይዘሮ ክብነሽ ኢዶሳ ናቸው፡፡

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ፣ የኮሪደር ልማትና ገበታ ለአገርን የመሳሰሉ ታሪክ ቀያሪ አገራዊ ፕሮጀክቶች በለውጡ መንግስት የተከናወኑ የልማት ስራዎች ናቸው ብለዋል፡፡

''በእርዳታና ብድር የባከነው ጊዜ በቃ ሊባልና! ሊቆጨን ይገባል! ሰርቶ የመለወጥ ባህልን ለማዳበር ራስን ማዘጋጀት ይኖርብናል'' ሲሉም አክለዋል፡፡

የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በተጀመረው ተስፋ ሰጪ የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት በተገኘው ውጤትም ኩራት እንደተሰማቸው ተናግረዋል።

አቶ አብዲ ኑር በበኩላቸው በለውጡ ዓመታት በምስራቅ ቦረና ዞን በርካታ የመሰረተ ልማት ግንባታ መከናወኑን አንስተው ከነዚህም ውስጥ የትምህርት፣ የጤና፣ የመጠጥ ውሀ፣ የመስኖ እና የመንገድ መሰረተ ልማት ፕሮጀክቶችን ለአብነት ጠቅሰዋል፡፡

ግንባታው ተጠናቆ ለምረቃ የተዘጋጀው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብም የአብሮነት መገለጫችን ብቻም ሳይሆን ህዝቡን በጠንካራ ሞራል ለስራ የሚያነሳሳ ነው ብለዋል፡፡

በምክክር መድረኩ ላይም የሀገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች ተሳትፈዋል፡፡

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም