ቀጥታ፡

ታላቁ የህዳሴ ግድብ የመንግሥትና የሕዝቡ የትብብር ውጤት ነው-አረጋዊ በርሄ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ነሐሴ 27/2017 (ኢዜአ)፡-ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ አይችሉም አይገነቡትም ያሉንን ያሳፈርንበት፤የለውጡ መንግሥትና የሕዝቡ የትብብር ውጤት ነው ሲሉ የህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አረጋዊ በርሄ (ዶ/ር) ገለጹ።

ዋና ሥራ አስፈጻሚ አረጋዊ በርሄ (ዶ/ር) ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለጹት፥ ታላቁ የህዳሴ ግድብ በለውጡ መንግሥትና የኢትዮጵያ ሕዝብ ትብብር ለውጤት በቅቷል።


 

ግድቡ እውን እንዲሆን በአገር ውስጥም በውጭም ያሉ ኢትዮጵያዊያን የገንዘብና የጉልበት ድጋፍ ከማድረግ ባለፈ በሞራል ያደረጉት ድጋፍ የሚመሰገን ነው ሲሉም ተናግረዋል።

ህዳሴ ግድቡ የገጠር ኢንዱስትሪዎችን ጨምሮ ትልልቅ ኢንዱስትሪዎችን ለማቋቋም ያለው አገራዊ አበርክቶ ትልቅ መሆኑን ጠቁመው፥ኢኮኖሚያዊ ዕድገትን ለማሳለጥ ወሳኝ ሚና እንደሚጫወትም ገልጸዋል።

እንደ ዋና ሥራ አስፈጻሚው ገለጻ፥ለታላቁ ህዳሴ ግድብ እውን መሆን የለውጡ መንግሥት ከሕዝቡ ጋር በመተባበር የተደረገው የተቀናጀ ርብርብ የላቀ ድርሻ ተጫውቷል።

"ግድቡ ኢትዮጵያዊያን ከተባበርን የማንገፋው ተራራ እንደሌለ ማሳያ ነው" ያሉት አረጋዊ በርሄ (ዶ/ር) በግድቡ ግንባታ የተገኘው ውጤት ሌሎች የልማት ፕሮጀክቶችንም በብቃት መፈጸም እንደምንችል ትምህርት የሰጠ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያዊያን በሌሎች ልማቶች ላይም የሚኖራቸው ተሳትፎ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታን በራስ አቅም ያለ ብድርና ዕርዳታ ማጠናቀቃችን ግድቡን መገንባት አይችሉም ያሉንን ያሳፈርንበት ነው ሲሉም ገልጸዋል።

ዋና ስራ አስፈጻሚ አረጋዊ በርሄ (ዶ/ር) እንዳሉት፤ከታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ሌሎች የአፍሪካ አገራት ልምድ እየቀሰሙ ነው።

ታላቁ የህዳሴ ግድብ ለሌሎች የአፍሪካ አገራት የልማት እርሾ፤ የልማት በር እየሆነ ነው ያሉት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፤ግድቡ ኢትዮጵያ ቀጣናውን በሃይል ለማስተሳሰር የምታደርገውን ጉዞ የተቃና ያደርገዋል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም