በምስራቅ ሸዋ ዞን ከ80 ሺህ ሔክታር በላይ መሬት በቦሎቄ ልማት ተሸፍኗል

አዳማ፤ነሐሴ 27/2017(ኢዜአ)፦በምስራቅ ሸዋ ዞን በኩታ ገጠም የሚለማ ከ80 ሺህ ሔክታር በላይ መሬት በኤክስፖርት ቦሎቄ መሸፈኑን የዞኑ ግብርና ጽሕፈት ቤት ገልጿል።

ዞኑ ከ1 ነጥብ 8 ሚሊዮን ኩንታል በላይ የቦሎቄ ምርት ለማግኘት በትኩረት እየተሰራ መሆኑም ተገልጿል።

የዞኑ ግብርና ጽሕፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ አብነት ዘገዬ ለኢዜአ እንደገለፁት፤ አብዛኞቹ የዞኑ ወረዳዎች ለቆላ ጥራጥሬ ሰብሎች አመቺ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በዞኑ የግብርና የኤክስፖርት ምርቶች ላይ በትኩረት እየሰራን ነው ያሉት አቶ አብነት በተለይ የቦሎቄና የማሾ ሰብሎች በሰፊው እንደሚመረቱ ተናግረዋል።

በዚህም የዞኑ አርሶ አደሮች በማህበር ተደራጅተው በቦሎቄ ልማት ላይ በብዛት እንዲሳተፉ የማድረግ ስራ መሰራቱን ተናግረዋል።

በዚህም በዞኑ ከ80 ሺህ ሔክታር በላይ መሬት በኩታ ገጠም በኤክስፖርት ቦሎቄ ልማት መሸፈኑን ተናግረዋል።

አዳሚ ቱሉ፣ ጂዱ ኮሞቦልቻ፣ ቦሰት፣ ሎሜ፣ ፈንታሌ፣ ዱግዳና ቦራ ወረዳዎች የቦሎቄ ልማት በኩታገጠም በስፋት የለማባቸው ወረዳዎች መሆናቸው ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም