የኢትዮጵያ መከላከያ ማርችንግ ባንድ ቡድን የተሰጠውን አገር የማስተዋወቅ ተልዕኮ በስኬት አጠናቆ ተመልሷል-ሜጀር ጀኔራል እንዳልካቸው ወልደኪዳን - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ መከላከያ ማርችንግ ባንድ ቡድን የተሰጠውን አገር የማስተዋወቅ ተልዕኮ በስኬት አጠናቆ ተመልሷል-ሜጀር ጀኔራል እንዳልካቸው ወልደኪዳን

አዲስ አበባ፤ነሐሴ 27/2017(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ መከላከያ ማርችንግ ባንድ ቡድን የተሰጠውን አገር የማስተዋወቅ ተልዕኮ በስኬት አጠናቆ ተመልሷል ሲሉ የመከላከያ ሠራዊት ስነልቦና ግንባታ ዳይሬክተር ሜጀር ጀኔራል እንዳልካቸው ወልደኪዳን ገለጹ።
በሩሲያ ሞስኮ በተዘጋጀው የማርችንግ ባንድ ፌስቲቫል ላይ የተሳተፈው የኢትዮጵያ መከላከያ ማርችንግ ባንድ ቡድን ዛሬ ጠዋት አዲስ አበባ ገብቷል።
ማርቺንግ ባንዱ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፈያ ሲደርስ ደማቅ አቀባበል ተደርጎለታል።
የመከላከያ ሠራዊት ስነልቦና ግንባታ ዳይሬክተር ሜጀር ጀኔራል እንዳልካቸው ወልደኪዳን በወቅቱ፣ የማርችንግ ባንድ ቡድኑ አባላት ተልዕኳቸውን በአግባቡ ያሳኩ የሀገር ጀግኖች መሆናቸውን ተናግረዋል።
በዓለም አቀፍ መድረክ ኢትዮጵያን በአግባቡ በማስተዋወቅ የሀገር መከላከያ ሠራዊትን እና ሀገርን ያኮራ ተግባር ማከናወናቸውን በመጥቀስ፥ እንኳን ደስ ያላችሁ ብለዋል።
የሀገር ኩራት መሆኑን ከዚህ ቀደም በብዙ ሥራዎቹ ያስመሰከረው የመከላከያ ማርችንግ ባንድ፥ በፌስቲቫሉ ላይ ያሳየው ሙያዊ ዲሲፒሊን ለዓለም አብነት የሚሆን ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ ሩሲያ ባዘጋጀችው ዓለም አቀፍ የመከላከያ ማርችንግ ባንድ ፌስቲቫል ላይ መሳተፏ ወታደራዊ የልምድ ልውውጥ ለማድረግና ትብብርን ለማጠናከር ጉልህ አበርክቶ መጫወቱን ተናግረዋል።
የመከላከያ ኪነ-ጥበባት ሥራዎች ዳይሬክተር ኮሎኔል ማንያህለዋል ታደለ ዝግጅቱ የተሳካ መሆኑን ጠቅሰው፥ ከአፍሪካ፣ ከአውሮፓ እና ከኤስያ የተወጣጡ የበርካታ ሀገራት የማርችንግ ባንድ አባላት መሳተፋቸውን ተናግረዋል።
ዘመናዊ የሙዚቃ መሳሪያን ተጠቅመን ባህላዊ ዘፈኖቻችንን እና ባህላዊ ጭፈራዎቻችንን አዋህደን በማቅረብ ዓለምን ያስደነቀ ሥራ ሠርተናል ብለዋል።
የማርችንግ ባንዱ ሉዑክ አባል የሆነችው ሻምበል ሔለን አለሙ፤ መድረኩ ልምዳችን ያካፈልንበት እና ከእነሱም ልምድ የወሰድንበት ነበር ብላለች፡፡
ሌላኛዋ የባንዱ ሉዑክ አባል ሐምሳ አለቃ ሒወት አሰፋ፤ ፌሰቲባሉ የአገራችን ባህልና ወግ ለአለም ከማስተዋወቅ ባሻገር ሩሲያውያን በአገራቸው ጉዳይ በአንድ ልብ መካሪ በአንድ ቃል ተናጋሪ መሆናቸውን አይተናል ብላለች።