ዩኒቨርሲቲው በአራት የትምህርት መርሃ ግብሮች ዓለም አቀፍ እውቅና አገኘ

አዲስ አበባ፤ነሐሴ 27/2017(ኢዜአ)፦የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ  በአራት የትምህርት መርሃ ግብሮች ዓለም አቀፍ እውቅና ማግኘቱን የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ደረጀ እንግዳ (ዶ/ር) ገለጹ።

ዶክተር ደረጀ እንግዳ እውቅናውን አስመልክተው ለመገናኛ ብዙሃን ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በማብራሪያቸውም ዩኒቨርሲቲው የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥና የሚሰጣቸው የትምህርት መርሃ ግብሮች ዓለም አቀፍ እውቅና ያላቸው እና ተወዳዳሪ እንዲሆኑ እየሰራ ይገኛል ብለዋል።

በዚህም  ዩኒቨርሲቲው አሜሪካ ከሚገኘው ዓለም አቀፍ የኢንጅነሪንግና ቴክኖሎጂ እውቅና ሰጭ ቦርድ  /ABET/ በአራት የትምህርት መርሃ ግብሮች እውቅና ማግኘቱን አስታውቀዋል።

እውቅናውን ያገኘው በመጀመሪያ ዲግሪ በሚሰጣቸው የባዮ-ቴክኖሎጂ፣ የምግብ ሳይንስ እና ሥነ ምግብ፣ የኢንዱስትሪያል ኬሚስትሪ እና የጂኦሎጂ የትምህርት መርሃ ግብሮች መሆኑን ጠቅሰዋል።

እውቅናው ለተመራቂ ተማሪዎች በዓለም አቀፍ ደረጃ የሥራ ዕድሎችን እንደሚከፍት እና የትምህርት መረጃቸው ዓለም አቀፍ እውቅና እንዲኖረው የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።

በተጨማሪም ዩኒቨርሲቲው ከመላው ዓለም ተማሪዎችን ተቀብሎ እንዲያስተምር ያስችለዋል ብለዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም