ኢትዮጵያን ከተረጂነት ለማላቀቅ የሚያስችል መሠረት ተጥሏል-ሚኒስትር ለገሠ ቱሉ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ነሐሴ 27/2017 (ኢዜአ)፡-ኢትዮጵያን ከተረጂነት ለማላቀቅ የሚያስችል መሠረት መጣሉን የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡ 

የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) ወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮችን አስመልክቶ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

ባለፉት ሰባት የለውጥ ዓመታት ኢትዮጵያ በተከተለችው የልማት መንገድና በአካታች የዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ በርካታ ድሎችና እመርታዎች መመዝገቡን ተናግረዋል፡፡

በዘላቂ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም በመመራት ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ፤ የምግብ ሉዓላዊነትን በማረጋገጥ፤ ኢትዮጵያን ከተረጂነት ለማላቀቅ የሚያስችል መሠረት መጣሉንም ገልጸዋል፡፡

በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ከውጭ ይገቡ የነበሩ በርካታ የኢንዱስትሪ ምርቶች መተካታቸውን፤ በተቀናጀ የፊስካል ፖሊሲ ከአስቸጋሪ የፋይናንስ ውዝፍ ችግር በመውጣት  ወደ ተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ለውጥ መሸጋገር መቻሉንም ተናግረዋል፡፡

በታዳሽ ኃይል ማመንጫ ግንባታ ታሪክ በብዙዎች ዘንድ አይችሉም የተባለበት ምዕራፍ የተዘጋበት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ 

ኢትዮጵያውያን በደማችን፤ በላባችን እና በአንጡራ ሀብታችን የታላቁ ህዳሴ ግድብን በለውጡ ዓመታት ከነበረበት ቅርቃር በማውጣት ማጠናቀቅ መቻሉን ተናግረዋል፡፡

እየተጠናቀቀ ባለው ዓመት ኢትዮጵያ በከፍታ ጉዞ ማንሰራራት የጀመረችበት መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

ባለፉት የለውጥ ዓመታት የጳጉሜን ቀናት በልዩ ልዩ ስያሜዎች ማክበር የተለመደ መሆኑን ጠቁመው፤  መጪዎቹ የጳጉሜን ቀናት በልዩ ልዩ ዝግጅቶች በመላ ሀገሪቱ እንደሚከበሩም ጠቁመዋል፡፡

በዚህም ጳጉሜን 1 ቀን የፅናት ቀን ተብሎ እንደተሰየመ ጠቁመው፤ "ፅኑ መሠረት ብርቱ ሀገር" በሚል መሪ መልዕክት እንደሚከበርም አብራርተዋል።

በፅናት ቀን ስለኢትዮጵያ ሰላምና ደኅንነት፣ ስለኢትዮጵያ ከፍታ' ስለኢትዮጵያ ብልጽግና ዘብ የቆሙ ጀግኖች ይታወሳሉ! ይወደሳሉ፣ ይመሰገናሉ ሲሉም ተናግረዋል፡፡

ጳጉሜን 2 ቀን የህብር ቀን በሚል ስያሜ "ብዝኃነት የኢትዮጵያ ጌጥ " በሚል መሪ መልዕክት እንደሚከበር ጠቁመው፤ ውበታችንን ለማሳየትና ለጥንካሬያችን መሠረት የሆኑ የአብሮነት እሴቶችን ይበልጥ ለማጉላት እንደሚውል አመልክተዋል።

ጳጉሜን ሦስት የእምርታ ቀን በሚል ስያሜ “እመርታ ለዘላቂ ከፍታ” በሚል መሪ መልዕክት እንደሚከበር ጠቅሰው፤ የእመርታ ቀን ባለፉት ዓመታት በተለያዩ መስኮች የተመዘገቡ ስኬቶች ዕውቅና የሚያገኙበት፤ ለቀጣይ ደግሞ የበለጠ መነሣሣት የሚፈጠርበት ቀን ነው ብለዋል፡፡

ጳጉሜን 4 የማንሰራራት ቀን በሚል ስያሜ "ዘላቂ ልማት ለሀገራዊ ማንሰራራት” በሚል መሪ ሀሳብ እንደሚከበር የገለጹት  ሚኒስትሩ፤ በዚህም  ባለፉት ዓመታት ለለውጡ መሠረት የጣሉ ተቋማትና የተመዘገቡ ስኬቶች እና ቀጣይ ተስፋዎች የሚተዋወቁበት ቀን መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

መንግሥት የጀመረው የብዝኃ ዘርፍ ኢኮኖሚ ዕሳቤዎች ውጤት ማምጣት የጀመሩበት፣ ለቀጣዩ የብልጽግና ጉዞ አስቻይ ተቋማት እና ሥርዓት የተፈጠረበት መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

2017 በጀት ዓመት ኢትዮጵያ ከነበሩባት ማነቆዎች በመላቀቅ ታሪክ ቀያሪ ድሎችን ማስመዝገብ የጀመረችበት ዓመት እንደነበርም ጠቁመዋል። 

ጳጉሜን 5 የነገው ቀን በሚል ስያሜ እንደሚከበር ጠቅሰው፤ ኢትዮጵያ ነገዋን ታሳቢ ያደረጉ እንደ አርተፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት፣ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት፣ ብሔራዊ መታወቂያ አገልግሎት፤ ሳይንስ ሙዚዬም ያሉ ተቋማትን ገንብታ ወደሥራ ማስገባቷን ጠቁመዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም