ሁሉም ኢትዮጵያዊ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅን አስመልክቶ ሀሳቡን የሚያጋራበት የአጭር መልዕክት ማስተላለፊያ ኮድ ይፋ ሆነ - ኢዜአ አማርኛ
ሁሉም ኢትዮጵያዊ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅን አስመልክቶ ሀሳቡን የሚያጋራበት የአጭር መልዕክት ማስተላለፊያ ኮድ ይፋ ሆነ

አዲስ አበባ፤ነሐሴ 27/2017 (ኢዜአ)፦ከዛሬ ጀምሮ ለ33 ቀናት የሚቆይ ሁሉም ኢትዮጵያዊ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅን በተመለከተ ያለውን ሃሳብና መልዕክት የሚያጋራበት 8120 አጭር መልዕክት ማስተላለፊያ ኮድ ይፋ ሆኗል።
የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ከኢትዮ-ቴሌኮም ጋር በመተባበር ዜጎች መልካም ምኞታቸውን የሚገልጹበት "የትውልድ አሻራ ዲጂታል የብስራት መልዕክትና ገቢ ማስገኛ ፕሮጀክት" በሚል ስያሜ መልዕክት እንዲያስተላልፉ የሚያስችል ነው።
በዚህ ወቅት የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አረጋዊ በርሄ (ዶ/ር) እንዳሉት፥ታላቁ የሕዳሴ ግድብ የወል ትርክታችንና ላባችንን ቀለም ክንዳችንን ደግሞ እንደብዕር አድርገን የፃፍነው መፅሀፍ ነው።
ሕዳሴ ግድብ ከተባበርን የዕድገት ማማ ላይ መውጣት እንደምንችል ማሳያ መሆኑን ተናግረዋል።
ህብረተሰቡ ለሕዳሴ ግድብ ግንባታ የበኩሉን ሲወጣ መቆየቱን ጠቁመው፤ ኢትዮ ቴሌኮም በ"8100 A" ላይ በመላክ በተከታታይ ለሶስት ዙር የድጋፍ ማሰባሰብ ስራ መሰራቱን ገልጸዋል።
ከዛሬ ጀምሮ ህብረተሰቡ ደስታውንና ስሜቱን የሚያጋራበት 8120 በእጅ ስልክ በመላክ መልዕክት ማጋራት ይችላል ነው ያሉት።
የአጭር መልዕክት ማስተላለፊያ ኮዱ ከዛሬ ነሃሴ 27 ቀን 2017 እስከ መስከረም 30 ቀን 2018 ድረስ ባሉት ጊዜያት ህብረተሰቡ ለታላቁ ሕዳሴ ግድብ እውን መሆን ሲያደርግ የነበረውን ድጋፍ በተመለከተ በአጭር መልዕክት ሃሳቡን በመግለፅ አሻራውን ለታሪክ መዘክርነት ማስቀመጥ የሚችልበት ነው።
በአጭር መልዕክት ማስተላለፊያ ኮዱ 1 ቁጥር መላክ አምስት ብር ድጋፍ ማድረግና በህብረት ችለናል የሚል መልዕክት ያለው ሲሆን፤ 2 ቁጥር ደግሞ የ10 ብር ድጋፍና ታላቁ ሕዳሴ ግድብ የብልፅግና አሻራ የሚል መልዕክት ያለው መሆኑ ተገልጿል።
3 ቁጥር የ15 ብር ድጋፍና ግድባችን የአሸናፊነት ድል አክሊል እንዲሁም 4 ቁጥር የ100 ብር ድጋፍና ግድባችን የአባይ ዘመን ትውልድ የተጋድሎ ሰንደቅ የሚል መልዕክት ያላቸው መሆኑ ተጠቁሟል።
በተጨማሪም ህብረተሰቡ የራሱን መልዕክት ሲልክ 20 ብር ድጋፍ እንደሚያደርግም ነው የተገለፀው።
እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ በታላቁ ሕዳሴ ግድብ ዙሪያ ያለውን ስሜት፣ሃሳብና መልዕክት ለታሪክ ከትቦ ማስቀመጥ የህዝባዊ ተሳትፎ አካል በመሆኑ ሁሉም ኢትዮጵያዊ መልዕክቱን በመግለፅ ለትውልድ የሚያስተላልፍበት ፕሮጀክት ማስፈለጉ ተገልጿል።