የመከላከያ ማርችንግ ባንድ በሩሲያ ቆይታው የሀገርን ባህል እና ሙያዊ ብቃቱን ለዓለም በማስተዋወቅ አኩሪ ተግባር ፈጽሟል-ሜጀር ጀነራል እንዳልካቸው ወልደኪዳን

አዲስ አበባ፤ነሐሴ 27/2017 (ኢዜአ)፦የመከላከያ ማርችንግ ባንድ ሩሲያ ባዘጋጀችው ዓለም አቀፍ የማርችንግ ባንድ ፌስቲቫል ላይ የሀገርን ባህልና ገፅታ እና ሙያዊ ብቃቱን ለዓለም በማስተዋወቅ አኩሪ ተግባር መፈጸሙን የመከላከያ ሠራዊት ስነልቦና ግንባታ ዳይሬክተር ሜጀር ጀነራል እንዳልካቸው ወልደኪዳን ገለጹ።

በሩሲያ ሞስኮ በተዘጋጀው የማርችንግ ባንድ ፌስቲቫል ላይ የተሳተፈው የኢትዮጵያ መከላከያ ማርችንግ ባንድ ቡድን ዛሬ ጠዋት አዲስ አበባ ገብቷል።


 

ማርቺንግ ባንዱ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርስ ደማቅ አቀባበል ተደርጎለታል።

የመከላከያ ሠራዊት የስነልቦና ግንባታ ዳይሬክተር ሜጀር ጀኔራል እንዳልካቸው ወልደኪዳን በዚሁ ወቅት፣የማርችንግ ባንድ ቡድኑ አባላት ተልዕኳቸውን በአግባቡ ያሳኩ የሀገር ጀግኖች መሆናቸውን ተናግረዋል።

በዓለም አቀፍ መድረክ ኢትዮጵያን በአግባቡ በማስተዋወቅ የሀገር መከላከያ ሠራዊትን እና ሀገርን ያኮራ ተግባር ማከናወናቸውን በመጥቀስ፥ እንኳን ደስ ያላችሁ ብለዋል።

የሀገር ኩራት መሆኑን ከዚህ ቀደም በብዙ ሥራዎቹ ያስመሰከረው የመከላከያ ማርችንግ ባንድ፥ በፌስቲቫሉ ላይ ያሳየው ሙያዊ ዲሲፕሊን ለዓለም አብነት የሚሆን ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ ሩሲያ ለ5 ቀናት ባዘጋጀችው ዓለም አቀፍ የመከላከያ ማርችንግ ባንድ ፌስቲቫል ላይ መሳተፏ ወታደራዊ የልምድ ልውውጥ ለማድረግና ትብብርን ለማጠናከር ጉልህ አበርክቶ መጫወቱን ተናግረዋል።

የመከላከያ ኪነ- ጥበባት ሥራዎች ዳይሬክተር ኮሎኔል ማንያህለዋል ታደለ ዝግጅቱ የተሳካ መሆኑን ጠቅሰው፥ ከአፍሪካ፣ከአውሮፓ እና ከእስያ የተወጣጡ የበርካታ ሀገራት የማርችንግ ባንዶች የተሳተፉበት መሆኑን ተናግረዋል።

ዘመናዊ የሙዚቃ መሳሪያን ተጠቅመን ባህላዊ ዘፈኖቻችንን እና ባህላዊ ጭፈራዎቻችንን አዋህደን በማቅረብ ዓለምን ያስደነቀ ሥራ ሠርተናል ብለዋል።

የማርችንግ ባንዱ ቡድን መሪ ሌተናል ኮሎኔል ዘመቻ በዲ በበኩላቸው፥ ቡድኑ በሠራቸው የሙዚቃ ሥራዎች እና የመድረክ ላይ እንቅስቃሴዎቹ ከፍተኛ አድናቆት ማግኘቱን ገልፀዋል።

ቡድኑ የሀገራችንን ብሔሮች ብሔረሰቦች አለባበስ፣ ዜማ፣ ውዝዋዜና ሌሎች የጥበብ ባህሎች በማስተዋወቅ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ማበርከቱን ተናግረዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም