ቀጥታ፡

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ አይበገሬነትን ያሳየንበት የጽናት ተምሳሌት ነው

ሐረር፤ነሐሴ 27/2017 (ኢዜአ)፦ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ አይበገሬነትን ያሳየንበት የጽናት ተምሳሌት ነው ሲሉ በሀገር መከላከያ ሰራዊት የምስራቅ እዝ አባላት ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሰኔ 26 ቀን 2017 ዓ.ም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው በሰጡት ማብራሪያ በብዙ ልፋትና መስዋዕትነት የተገነባው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በመስከረም ወር እንደሚመረቅ ማብሰራቸው ይታወሳል፡፡

ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት አስተያየታቸውን የሰጡ የእዙ ሰራዊት አባላት እንደተናገሩት፥ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያውያን አይበገሬነት ማሳያ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

ከሰራዊቱ አባላት መካከል ሻምበል ካሰች ዓለሙ እንደተናገሩት፥ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን እንደ ልጄ የምመለከተውና እንደ ዓይኔ ብሌን የምቆጥረው ግድብ ነው።

መስዋትነት የተከፈለበትና በይቻላል መንፈስ የተገነባው ግድቡ እዚህ ደረጃ ላይ በመድረሱ ደስታ ፈጥሮብኛል ያሉት ሻምበል ካሰች፥ በቀጣይም መሰል የልማት ስራዎችን ተግባራዊ ለማድረግ ከፍተኛ መነቃቃትን ይፈጥራል ብለዋል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ኢትዮጵያውያን ተባብረው የገነቡትና መስዋዕትነት ከፍለው ለዚህ ያደረሱት ግድብ በመሆኑ ሁሌም ኩራት ይሰማኛል ያሉት ደግሞ ሻለቃ ምስክር ብርሃኑ ናቸው።

ግድቡ በፈተናዎች ውስጥ እንዴት ማሸነፍ እንደምንችል ያሳየንበት የጽናት ተምሳሌት ነው ሲሉም አክለዋል።

ኮሎኔል ተፈራ ማርቆስ በበኩላቸው፥ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በኢትዮጵያውያን አቅም የተገነባ የሀገር ቅርስ ነው ብለዋል።

በግድቡ ግንባታም የሰራዊቱ ሚና ከፍተኛ እንደነበር ያስታወሱት ኮሎኔል ተፈራ፥ በተለይ ግድቡ ለዚህ ደረጃ በመድረሱ ከፍተኛ ደስታ እንደፈጠረባቸው ተናግረዋል።

ግድቡ የኢትዮጵያውያን የሕብረት፣የጽናት እና የይቻላል መንፈስ በተግባር የታየበት ነው ያሉት ደግሞ ምክትል አስር አለቃ ይገርማል አላምረው ናቸው።

ግድቡ በተለይም ለሠራዊቱ ልዩ ትርጉም ያለው ነው ሲሉም ተናግረዋል።

በሀገር መከላከያ ሰራዊት የምስራቅ እዝ 48ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን በተለያዩ ሁነቶች እያከበረ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም