ኢትዮጵያውያን በተደመረ አቅም እና የአላማ ጽናት ታላቁ የህዳሴ ግድብ እንዲጠናቀቅ አድርገዋል -ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያውያን በተደመረ አቅም እና የአላማ ጽናት ታላቁ የህዳሴ ግድብ እንዲጠናቀቅ አድርገዋል -ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ነሐሴ 26/2017 (ኢዜአ)፦ኢትዮጵያውያን በተደመረ አቅም እና የአላማ ጽናት በራሳቸው ገንዘብ ታላቁ የህዳሴ ግድብ እንዲጠናቀቅ አድርገዋል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከጠቅላይ ሚኒስትሩ የማህበራዊ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር ሙአዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ጋር የ“ኩስመና ታሪክ ማብቂያ” በሚል ርዕስ የጉባ ላይ ወግ አድርገዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ሂደት እጅግ አታካች፣አድካሚ፣ አሰልቺ፣አጨቃጫቂ እና የአላማ ጽናትን የፈተነ እንደነበር አውስተዋል።
የገንዘብ ድጋፍ አለማግኘት፣የዲፕሎማሲ ጫና፣ ኮቪድ-19 ወረርሽኝ፣ የቀይ ባህር ውጥረት እና ሌሎች ፈተናዎች ተደራርበው ግንባታውን በፈተና የተሞላ አድርገውት እንደነበር ገልጸዋል።
ኢትዮጵያውያን በተደመረ አቅም እና የአላማ ጽናት በራሳቸው ገንዘብ በመስራት ግድቡ እንዲጠናቀቅ ማድረጋቸውንም አመልክተዋል።
በዚህም ግድቡ የነበረውን ቁጭት እና እሮሮ ከማስቀረት ባሻገር ብርሃን ማግኘት መቻሉን ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የገለጹት።
ከዚህ ግድብ ብርሃን ነው የወጣው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ለብዙ ጨለማ ለወረሳቸው እና በድህነት ላሉ ህዝቦች ብርሃንን መፈንጠቁን አመልክተዋል።
የግድቡ መጠናቀቅ ለኢትዮጵያ፣ለቀጣናው እና ለወንድሞቻችን ትልቅ ብስራት ነው ሲሉ ተናግረዋል።
ብስራቱን ለማየት የወሰደው ጊዜ ረጅም ቢሆንም የተገኘው ፍሬ እጅግ በጣም ጣፋጭ እንደሆነ ገልጸዋል።