የምስራቅ ኢትዮጵያ ተጎራባች ክልሎችን የሰላም እሴቶች ግንባታ ይበልጥ ለማጠናከር ትኩረት ተሰጥቷል - ኢዜአ አማርኛ
የምስራቅ ኢትዮጵያ ተጎራባች ክልሎችን የሰላም እሴቶች ግንባታ ይበልጥ ለማጠናከር ትኩረት ተሰጥቷል

ድሬደዋ፤ነሐሴ 27/2017(ኢዜአ)፡-የምስራቅ ኢትዮጵያ ተጎራባች ክልሎችን የሰላም እሴቶችን ግንባታ ይበልጥ ለማጠናከር ትኩረት መሰጠቱ ተገልጿል።
የምስራቅ ኢትዮጵያ ተጎራባች ክልሎችን የሰላም እሴቶችን ግንባታና ግንኙነትን ይበልጥ ለማጠናከር የሚያስችል የምክክር መድረክ በድሬደዋ እየተካሄደ ነው።
የምክክር መድረኩን የፌደሬሽን ምክር ቤት ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም ጋር በመተባበር ያዘጋጀው ነው።
የፌደሬሽን ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ ዘሐራ ሁመድ እና የሰላም ሚኒስቴር ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተዋል።
በተጨማሪም የምስራቅ ተጎራባች ክልሎች የሆኑት የሶማሌ፣ የአፋር፣ የሐረሪ፣ የምስራቅና ምዕራብ ሐረርጌ ኦሮሚያ ዞኖችና የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤቶች አፈ ጉባኤዎች እንዲሁም የፀጥታ ዘርፍ ሀላፊዎች እየተሳተፉ ነው።
በቀጠናው ያለውን ዘላቂ ሰላም ለማፅናት እና የተጎራባች ክልሎቹን የመንግስታት ግንኙነት ለማጠናከር ያለመ መድረክ መሆኑን የፌደሬሽን ምክር ቤት የህዝብ ግንኙነትና የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ተወካይ አቶ ሞገስ ጀምበሬ ለኢዜአ ገልጸዋል።
እንደ አቶ ሞገስ ገለፃ፥ ተጎራባች ክልሎቹ የፈጠሩትን የጋራ ፎረም በማጎልበት በአካባቢው ተቀናጅተው የጀመሩትን የብልፅግና ጉዞ ለማጠናከር ያግዛቸዋል።