ቀጥታ፡

የህዳሴ ግድብ በየዓመቱ እስከ አንድ ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ገቢ ያስገኛል ተብሎ ይጠበቃል-ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 27/2017 (ኢዜአ)፦ ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በየዓመቱ አንድ ቢሊዮን ዶላር ገደማ ገቢ ይገኝበታል ተብሎ እንደሚጠበቅ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።

ህዳሴ ግድብ ኢትዮጵያ ባጠረ ጊዜ ውስጥ ብልጽግናን ማረጋገጥ እንደምትችል የሚያሳይ ነውም ብለዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማህበራዊ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር ሙአዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጋር የ“ኩስመና ታሪክ ማብቂያ” በሚል ርዕስ የጉባ ላይ ወግ አድርገዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አባይ ማደሪያ የለውም ግንድ ይዞ ይዞራል የሚለው ታሪክ ማክተሙን ገልጸዋል።

ህዳሴ ግድብ ከኢነርጂ ምርት ባለፈ ዘርፈ ብዙ የኢኮኖሚ ጠቃሜታዎች እንዳሉት አመልክተዋል።

ከግድቡ በየዓመቱ አንድ ቢሊዮን ዶላር ገደማ ገቢ ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅ የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህም ለግድቡ የወጣውን ወጪ በተወሰኑ ዓመታት ውስጥ እንደሚመልስ ተናግረዋል።

በመተባበር እና በመደመር እንዲሁም የኢትዮጵያ እምቅ ሀብቶች በሚገባ በመጠቀም ለቀጣዩ ትውልድ እና ሌሎችም እንዲተርፍ ለማድረግ በጋራ መስራት ይገባል ነው ያሉት።

ከምናየው እና ከምንሻው የሩቁ ህልማችን ላይ አይናችን ሳይነቀል ተግተን በተደመረ አቅም ከተሰራ የኢትዮጵያን ብልጽግና ባጠረ ጊዜ ማሳካት እንደሚቻል ገልጸዋል።

በዚህ ረገድም ህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያ ብልጽግና እውን ማድረግ እንደሚቻል የሚያሳይ ፕሮጀክት እንደሆነ አንስተዋል።

የኢትዮጵያን ፍላጎቶች እና ጥቅሞች የማይደራደር ትውልድ እንዲፈጠርና ከሌሎች ጋር በጋራ ተጠቃሚነት መርህ ግንኙነታችንን ማስጠበቅ እንዲቻል አበክሮ መስራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

ኢትዮጵያውያን የህዳሴ ግድብ በመጠናቀቁ እንኳን ደስ አላችሁ ሲሉ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ህዝቡ የታሪክ አሻራውን ያሳረፈበትን ግድብ እንዲጎበኝ ጥሪ አቅርበዋል።

ኢትዮጵያ በቀጣይ ትላልቅ ፕሮጀክቶችን በመገንባት ህልሟን እውን ለማድረግ እንደምትሰራም አክለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም