በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ላይ ያለው ሐይቅ ስያሜ “ንጋት” ብለነዋል - ኢዜአ አማርኛ
በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ላይ ያለው ሐይቅ ስያሜ “ንጋት” ብለነዋል

አዲስ አበባ፤ነሐሴ 27/2017 (ኢዜአ)፡-በታላቁ ኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ላይ ያለው ሐይቅ ስሜ “ንጋት” እንዲባል መወሰኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አስታወቁ።
"የኩስመና ታሪክ ማብቂያ" በሚል ርዕስ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ባደረጉት የጉባ ላይ ወግ፤ በታላቁ የሕዳሴ ግድብ ላይ ያለው ሐይቅ በኢትዮጵያ ትልቁ ነው፤በአፍሪካም ከትላልቆቹ ሐይቆች አንዱ ነው ብለዋል።
አሁን ላይም 74 ትሪሊየን ሊትር ውኃ መያዙን ጠቅሰው፤ በሕዳሴው ግድብ ያለውን ሐይቅ ከእንቅልፍ የነቃንበት ዘመን በመሆኑና ስያሜው የወል እንዲሆን በማሰብ “ንጋት” ብለነዋል ሲሉ አስታውቀዋል።
ንጋት ማለት ረዥሙ ጨለማ አልቆ ጎኅ ሲቀድ፣ የብርሃን ፍንጣቂ መታየት ሲጀምር ያለው ጊዜ መሆኑንም አስረድተዋል።
ንጋት ከፊታችን ብርሃን መምጣት ያሳያል፤የውሏችን እንቅስቃሴ የሚጀመርበት ጊዜም ነው ብለዋል።
ያለንበት ወቅት የኢትዮጵያ የማንሰራራት ዘመን መሆኑን እኛ ብቻ ሳንሆን ዓለም ከዓባይ ጋር የሚመሰክረው ነው ብለዋል።