የህዳሴ ግድብ የአባይን የዘመናት ህልም ወደ ፍሬ ማፍራት እንዲሸጋገር አድርጓል-ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
የህዳሴ ግድብ የአባይን የዘመናት ህልም ወደ ፍሬ ማፍራት እንዲሸጋገር አድርጓል-ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ነሐሴ 26/2017 (ኢዜአ)፦የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የአባይን የዘመናት ህልም እና እንጉርጉሮ ወደ ሚጨበጥ ውጤት እንዲቀየር ማድረጉን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማህበራዊ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር ሙአዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጋር የ“ኩስመና ታሪክ ማብቂያ” በሚል ርዕስ የጉባ ላይ ወግ አድርገዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ኢትዮጵያውያን ለበርካታ መቶ ዓመታት በአባይ ወንዝ ተጠቅሞ ለማደግ ፍላጎቶች እንደነበሯቸው እና ሙከራዎችን እንዳደረጉ አመልክተዋል።
ሙከራዎቹ በገንዘብ እጥረት፣በቴክኒክ አቅም ውስንነት፣ የጂኦ ፖለቲካ አለመመቸት እና ብዙ ምክንያቶች ሙከራዎቹን እንዳይሳኩ ማድረጉን ተናግረዋል።
አባይን አስመልክቶ ያሉ በርካታ ስነ ጽሁፎች፣ ግጥሞች፣ ዘፈኖች እና እንጉርጉሮዎች በሀብቱ መጠቀምን ሳይሆን ባለመጠቀም ውስጥ ያለን ቁጭት አጉልተው የሚያሳዩ ናቸው ብለዋል።
በወንዙ ሀብት ተጠቅሞ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግንባታ ማከናወን የተቻለው ከጂኦ ፖለቲካዊ ኩስመና ወደ ተሻለ ቁመና ሽግግር ውጤት መሆኑን ነው የገለጹት።
መንግስት ጂኦ ፖለቲካዊ ኩስመና በፍጹም አንቀበልም እኛን አይመጥነንም፣ ኢትዮጵያ ካላት ስፋት አንጻር ለህዝቡ ታሪክ የሚበጅ አይደለም በማለት ትርክቱን ለመቀየር ወደ ስራ መግባቱን አመልክተዋል።
በጂኦ ፖለቲክሱ የተሻለ ቁመናን ለመያዝ እየተከናወነ ባለው ስራ እና ሌሎች አስቻይ ሁኔታዎች ምክንያት የዘመናት ህልም፣የዘመናት እንጉርጉሮና የዘመናት ለቅሶ ወደ ፍሬና ወደ ውጤት እንዲቀየር ማስቻሉን ተናግረዋል።
#Ethiopian_News_Agency
#ኢዜአ
#Ethiopia
#ኢትዮጵያ
#ህዳሴ
#የአባይግድብ