ሕዳሴን እንደ መደበኛ ፕሮጀክት ሳይሆን እንደ የዘመናት ቀንበር መስበሪያ፤እንደ የታሪክ መታጠፊያ መስመር አድርጌ ነው የማየው-ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)


አዲስ አበባ፤ነሐሴ 26/2017 (ኢዜአ)፡-ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የሕዳሴ ግድብን እንደ መደበኛ ፕሮጀክት ሳይሆን የዘመናት ቀንበር መስበሪያ፤የታሪክ መታጠፊያ መስመር አድርጌ ነው የማየው አሉ።

"የኩስመና ታሪክ ማብቂያ" በሚል ርዕስ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከጠቅላይ ሚኒስትሩ የማህበራዊ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር ሙአዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት  ጋር ባደረጉት የጉባ ላይ ወግ፤ከሕዳሴው ግድብ ፕሮጀክት ክትትልና ስኬታማ አፈጻጸም ጋር በተያያዘ ገለጻ አድርገዋል።

በገለጻቸውም፤አንድን ሥራ ጀምሮ ለመጨረስ፤በቅድሚያ ጨርሶ የማየት ዐቅም ያስፈልጋል ብለዋል።

ያንን ቀድመን ጨርሰን ያየነውን ነገር በርካቶች እንዲያዩት ደግሞ በከፍተኛ ዲሲፕሊን መትጋት ይፈልጋል ነው ያሉት።

በዚሁ መሠረት ላለፉት ሰባት ዓመታት ወደ ታላቁ የሕዳሴ ግድብ በመመላለስ በንቃት ክትትል ማድረጋቸውን አንስተዋል።

የክትትል ሥራ ለማንኛውም የሥራ መሥክ ወሳኝ መሆኑን ገልጸው፤የተጉ እናቶች ልጆጃቸውን ለፍሬ እንዳበቁ ሁሉ፤ የተጉ ሠራተኞች ደግሞ ሀገራቸውን ለፍሬ አብቅተዋል፤ ኢትዮጵያ ውስጥ እየሆነ ያለውም ይህ ነው ብለዋል። 

የሕዳሴ ግድብን እንደ መደበኛ ፕሮጀክት ሳይሆን የዘመናት ቀንበር መስበሪያ፤ የታሪክ መታጠፊያ መስመር አድርጌ ነው የማየው ሲሉም ገልጸዋል።

እንደሚታወቀው ዓባይ ለዘመናት ሲሄድብን ኖሯል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ የሕዳሴ እሳቤ ውኃ እንዲሄድብን ሳይሆን ጀልባ ሠርተን እኛ በውኃ ላይ እንድንሄድበት ነው፤በዚህም ዓሣ ማጥመድ እንድንችል ነው፤ ያስቀረነውን አፈር መርምረን ወርቅ ይኑረው ወይም አይኑረው መለየት እንድንችል ነው ሲሉ አብራርተዋል።

ዓባይን ጨርሶ ኢትዮጵያ ውስጥ የታሪክ እጥፋት ማረጋገጥ የመጨረሻ ጸሎቴና ምኞቴ ነበር ሲሉም ገልጸዋል።

ሲጀመር ፈጣሪ ትልቁን ዓባይ ለኢትዮጵያ አምኖ የሰጠው በፍትሐዊነት እንደምትጠቀመው ስላመነባት ነው ብዬ አምናለሁ ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።

በዚህ አግባብ ነው ግድባችንን ለፍሬ ያበቃነው፤በሱዳንም ሆነ በግብጽ ያሉ ግድቦች አንድም ሊትር አልቀነሱም በቂ መረጃ አለን፤ ወደ ፊትም እንዳይቀንሱ ነው የእኛ ፍላጎት በዚሁ አግባብ እንሠራለን ብለዋል።

ከተደመርን እና ከተጋን ያሰብነው ይሳካል፥ ለዚህም የሕዳሴው ግድብ ማሳያ ነው በማለት ጠቅሰዋል።
 #Ethiopian_News_Agency #Ethiopia #ኢትዮጵያ #ኢዜአ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም