ቀጥታ፡

የንግድ ምህዳሩን ምቹ ለማድረግ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ -ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ( ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ነሐሴ 26/2017 (ኢዜአ)፡-የንግድ ምህዳሩን ለሸማቾች እና ንግዱ ማህበረሰብ ምቹ ለማድረግ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) ገለጹ።

"የኢትዮጵያን  ይግዙ"  የንግድ ሳምንት ኤክስፖ 2017 መገናኛ በሚገኘው የጥራት መንደር እየተካሄደ ሲሆን እስከ ነሐሴ 29 ቀን 2017 ዓም ድረስ ክፍት ሆኖ ይቆያል።

ከኤስፖው ጎን ለጎን  የሀገር ውስጥ ንግድ ላይ ትኩረት ያደረገ  የፓናል ውይይት ዛሬ ተካሂዷል። 


 

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር)  በወቅቱ እንዳሉት፤ የንግድ ምህዳሩን ለሸማቾች እና ንግዱ ማህበረሰብ ምቹ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ ይገኛል።  

በዚህም የሸማች እና የንግድ ማህበረሰቡ እርካታ እያደገ መምጣቱን ጠቁመው በቀጣይ ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው አንስተዋል።  

እንደ ሚኒስትሩ ገለጻ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 3 ሚሊዮን 25 ሺህ ተገልጋዮች የኦንላይን ንግድ ምዝገባና ፈቃድ አገልግሎት መሰጠቱን ተናግረዋል።    

ለገበያ መሰረተ ልማት መስፋፋት ትኩረት መሰጠቱን የተናገሩት ሚኒስትሩ፤ ገበያውን ለማረጋጋት ከፍ ያለ ፋይዳ ያላቸው በርካታ የቅዳሜ  እና  እሁድ ገበያዎች ወደ ስራ እንዲገቡ መደረጉንም አመልክተዋል።

ሚኒስትሩ እንዳሉት፣ ከህግና ስርዓት ውጪ የሚንቀሳቀሱ ላይም የሚወሰደው እርምጃ  መቀጠሉንም ጠቅሰዋል።

ለአብነትም በ2017 በጀት ዓመት 110 ሺህ ህገ ወጥ ድርጊት የፈጸሙ ነጋዴዎች ላይ አስተዳደራዊና ህጋዊ እርምጃ መወሰዱን ተናግረዋል።  

የንግዱን ዘርፍ ምቹ ለማድረግ በሚደረገው ጥረት የባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን ገልጸው፤ መሰል የውይይት መድረክ በዘርፉ ያሉ ችግሮችን ለይቶ የመፍትሔ አቅጣጫዎችን ለማመላከት የላቀ ድርሻ እንዳለው ተናግረዋል። 


 

የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ሶፊያ ካሳ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ምርቶች በአግባቡ ለሸማቾች ቀርበው ንግድ እንዲሳለጥ የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ ሊጠናከር እንደሚገባ ጠቁመዋል።     

በዚህም የግሉ ዘርፍ በግብርናው ኢንቨስትመንት ተሳትፎን ከማሳደግ ባለፈ በቴክኖሎጂና ሌሎች የግበዓት አቅርቦቶች ላይ በተሻለ መልኩ ሊሳተፉ እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል። 

የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኀበራት ምክር ቤት ዋና ጸሃፊ ተባባሪ ፕሮፌሰር ቀነኒሳ ለሚ(ዶ/ር) እንደገለጹት፤ ዘመናዊ የንግድ ሥርዓትን ለመዘርጋት አስቻይ የሕግና የፖለሲ ማዕቀፎች ማውጣት ላይ የበለጠ ሊሰራ ይገባል።  

ለንግዱ መሳለጥ የመሰረተ ልማት አቅርቦት ቁልፍ ጉዳይ ነው ያሉት ዋና ጸሃፊው ፤ የሰው ኃይል አቅም ግንባታ ጉዳይም ትኩረት የሚፈልግ መሆኑን አብራርተዋል።  

የኢትዮጵያ ነጋዴ ሴቶች ማኀበር ፕሬዝዳንት ወይዘሮ በረከት ወርቁ በበኩላቸው፤ በሸማችና በአምራች መካከል ያለውን የግብይት ሰንሰለት ለማሳጠር በመንግሥት የተወሰዱ እርምጃዎች አበረታች መሆኑን ጠቁመዋል። 

የኢትዮጵያ ሸማቾች መብት ተቆርቋሪ ድርጅት መሥራችና ሥራ አስኪያጅ አቶ ቁምላቸው አበበ የንግድ ሥርዓቱን ጤናማ ለማድረግ ሸማቾች ባላቸው መብት ዙሪያ ተገቢውን ግንዛቤ እንዲጨብጡ ማድረግ ትልቅ ሚና አለው ብለዋል። 

ከሕግና ሥርዓት ውጪ የሚንቀሳቀሱ ነጋዴዎች ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ሊወጡ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ በጥራት መንደር የተዘጋጀውን "የኢትዮጵያን ይግዙ" ሀገራዊ የንግድ ሳምንት ኤክስፖ ነሐሴ 24 ቀን 2017 ዓም መርቀው መክፈታቸው ይታወቃል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም