የሚያጋጥሙ ፈተናዎችን በፅናት በማለፍና ወደ ዕድል በመቀየር የብልጽግና እሳቤዎች ወደ ውጤት እየተቀየሩ ነው- አቶ አደም ፋራህ

ሀዋሳ ፤ነሐሴ 26/2017 (ኢዜአ) ፡-የሚያጋጥሙ ፈተናዎችን በፅናት በማለፍና ወደ ዕድል በመቀየር የብልጽግና እሳቤዎች ወደ ውጤት እየተቀየሩ መሆኑን የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንትና በምክትል ጠቅላይ ሚንስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ሀላፊ አቶ አደም ፋራህ ገለጹ።

በሲዳማ ክልል እየተከናወኑ ያሉ የልማት ሥራዎች ለትውልድ ቅርስ የሚሆኑና ነገን ታሳቢ ያደረጉ መሆናቸውም ተመላክቷል።

አቶ አደም ፋራህ በሲዳማ ክልል ደራራና ሎካ አባያ ወረዳዎች እንዲሁም በሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ቱላ ክፍለ ከተማ በፓርቲው አባላትና ደጋፊዎች ሙሉ ወጪ የተገነቡ የብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤቶችን ዛሬ መርቀው ሥራ አስጀምረዋል።


 

በምረቃ ስነስርዓቱ ላይ አቶ አደም ፋራህ እንዳሉት በፈተና አለመሸነፍ፣ በተግዳሮት አለመበገርና ፈተናን ወደ ዕድል ቀይሮ የስኬት ጉዞን የማስቀጠል የፓርቲው እሳቤዎች በውጤታማነት ተግባራዊ መሆን ጀምረዋል። 

ለዚህም የሲዳማ ክልል ማሳያ እንደሆነ በተግባር አይተናል ብለዋል።

የሲዳማ ክልል በብልጽግና እሳቤዎች በመመራት ፈተናን ወደ ዕድል ከመቀየር ባለፈ ቤተሰብን ማዕከል ያደረገ ዕቅድ በማውጣት ለሌሎች ተሞክሮ የሚሆን ሥራ ሰርቷል ብለዋል።

ፓርቲው በአጭር ጊዜ ውስጥ የኢትዮጵያን ብልጽግና ለማረጋገጥ እሳቤና የህዝብ ድጋፍ እንዳለው ገልጸው፣ "ይሄንን ማሳካት የሚቻለው በመንግስት አቅም ብቻ ሳይሆን የህዝብ አቅምን በመጠቀም ጭምር ነው” ብለዋል።

በሲዳማ ክልል እየተከናወኑ ያሉ የልማት ሥራዎችም ለትውልድ ቅርስ የሚሆኑና ነገን ታሳቢ ያደረጉ መሆናቸውን በጉብኝት ወቅት መመልከታቸውን ገልጸዋል።

በክልሉ በተለያዩ አካባቢዎች የተከናወኑ የልማት ሥራዎች ይህን ታሳቢ ያደረጉና በውጤታማነት እየተተገበሩ መሆናቸውን ገልጸው፣  አመራሩ ይህን ሥራ አጠናክሮ ማስቀጠል አለበት ሲሉ አሳስበዋል።

በየደረጃው ያለው ህብረተሰብ ከብልጽግና ፓርቲ ጎን በመሆን ላበረከተው ሁለንተናዊ አስተዋጾ አመስግነው በቀጣይ ለሚሰሩ የልማት ሥራዎችም ከፓርቲው ጎን በመቆም ድጋፉን እንዲያጠናክር ጥሪ አቅርበዋል።


 

የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ በበኩላቸው እንዳሉት ሲዳማ ክልል ከሆነ በኋላ ባሉት ዓመታት የህዝብን ፍላጎት መሰረት ያደረጉ መሰረተ ልማቶችን የማመሏት ስራዎች ተከናውነዋል።

ለዚህም የህዝቡን የመንገድ ጥያቄ ለመመለስ ከ1 ሺህ 200 ኪሎ ሜትር በላይ አዲስ መንገድ በመገንባት ለአገልግሎት እንዲበቃ መደረጉን  በማሳያነት ገልጸዋል።

ከንጹህ መጠጥ ውሀ አቅርቦት አንጻር ክልሉ ሲመሰረት 38 በመቶ የነበረውን ሽፋን በአሁኑ ወቅት 65 በመቶ ለማድረስ እንደተቻለም ጠቁመዋል።

ህዝብን ተጠቃሚ የሚያደርጉና የቤተሰብ ብልጽግናን እውን የሚያደርጉ የሌማት ትሩፋትና ሌሎች መርሀ ግብሮችን ተግባራዊ በማድረግ ውጤት እየተመዘገበ መምጣቱንም አስረድተዋል።

የክልሉን ህዝብ በማስተባበርና በማንቀሳቀስ ከ750 ሚሊዮን ብር በላይ በማሰባሰብ ከቅድመ መደበኛ እስከ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን መገንባት እንደተቻለና በቀጣይም በህዝብ ተሳትፎ በርካታ የልማት ስራዎች እንደሚከናወኑ ተናግረዋል።


 

በብልጽግና ፓርቲ የሲዳማ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሀላፊ አቶ አብርሀም ማርሻሎ በበኩላቸው በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች ከዛሬ ጀምሮ እየተመረቁ ያሉ የልማት ፕሮጀክቶች ወጪያቸው በፓርቲው አባላት፣ ደጋፊዎችና የተለያዩ አካላት ሙሉ ለሙሉ የተሸፈነ መሆኑን ተናግረዋል።

"በዚህም 43 የፓርቲ ጽህፈት ቤቶች መገንባታቸውንና ለግንባታውም ከ1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በጥሬና 200 ሺህ ብር በአይነት ለማሰባሰብ ተችሏል" ብለዋል።

በምረቃ ሥነስርዓቱ ላይ የብልጽግና ፓርቲ የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ኃላፊ ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር)፣ በብልጽግና ፓርቲ የዴሞክራሲ ባህል ግንባታ ዘርፍ ኃላፊ መለሰ ዓለሙን ጨምሮ ሌሎች የብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮችም ተገኝተዋል። 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም