ከ500 በላይ ሥራዎችን የሚያሳልጠው ጉበት … - ኢዜአ አማርኛ
ከ500 በላይ ሥራዎችን የሚያሳልጠው ጉበት …

ጉበት ከ500 በላይ ሥራዎችን የሚያከናውን ዋነኛ እና ሁለገብ የሰውነታችን አካል ነው ይላሉ በአለርት ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የውስጥ ደዌ ስፔሻሊስት እና የጨጓራ፣ አንጀት እና ጉበት ሰብ ስፔሻሊስት ዶክተር አብዲ ባቲ።
የጉበት ተግባራት በአራት ዐቢይ ክፍሎች እንደሚከፈሉም ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ አስረድተዋል።
👉 የመጀመሪያው ተግባሩ፤ ጎጂ ንጥረ ነገሮችን ከደም ውስጥ ማጽዳት፣ ቆሻሻ ምርቶችን ማስወገድ፣ የመድኃኒቶችን ሜታቦሊዝም ማከናወን፣ ከምንበላው፣ ከምንጠጣው እና ከምንተነፍሰው ሁሉ መርዞችን ማስወገድ ነው ይላሉ።
👉 እንዲሁም ሁለተኛው ተግባሩ፤ ቫይታሚኖችን፣ ማዕድናትን እና ኃይልን ማከማቸት መሆኑን ገልጸው፤ ለሰውነታችን ማበረታቻ ኃይል በሚያስፈልግበት ጊዜ ዝግጁ ማድረግ ነው ብለዋል።
👉 ሦስተኛው ተግባር ደግሞ፤ ለደም መርጋት እና ኢንፌክሽኖችን ለመዋጋት ፕሮቲኖችን ማመንጨት መሆኑን ያስረዳሉ።
👉 አራተኛው ተግባሩን ሲያብራሩም፤ ‘Bile’ የሚባል ንጥረ ነገር በማምረት ከሚወዷቸው (ከሚመገቧቸው) ምግቦች ውስጥ የሚገኘውን ስብ እንዲፈጭ ያደርጋል ሲሉ ገልጸዋል።
ጉበትን ለህመም የሚያጋልጡ መንስኤዎች ምንድን ናቸው?
• እንደ ዶክተር አብዲ ገለጻ፤ ጉበት ዘርፈ ብዙ ተግባራት ያለው ወሳኝ የሰውነት አካል እንደመሆኑ ለብዙ አደጋዎች ይጋለጣል። ከነዚህ አጋላጭ ምክንያቶች መካከል ከታች የተጠቀሱት ዋነኞቹ ናቸው ብለዋል።
👉 እንደ ሄፓታይተስ ቢ እና ሲ ባሉ ቫይረሶች በደም፣ በመርፌ ወይም ወሊድ ወቅት የሚተላለፉ፤
👉 ከመጠን በላይ አልኮል መጠቀም፤
👉 ከመጠን በላይ መወፈር ፤
👉 የስኳር በሽታ፤
👉 ከእፅዋት እና የተለያዩ እህሎች (ለምሳሌ ከማሽላ እና በቆሎ) ውስጥ የሚገኙ እንደ አፍላቶክሲን ያሉ መርዛማ ንጥረ ነገሮች ይገኙበታል ብለዋል።
👉 በተጨማሪም ከ40 ዓመት በላይ መሆን፣ በቤተሰብ የሚተላለፉ የጉበት በሽታዎች መኖር፣ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት እና አደገኛ ልማዶች ለጉበት በሽታ ከሚያጋልጡ መንስዔዎች መካከል ናቸው ይላሉ።
ከእነዚህ አጋላጭ መንስኤዎች አብዛኛዎቹ ሊወገዱ የሚችሉ እንዲሁም ቀድመን በማወቅ እና በመጠንቀቅ መከላከል የሚቻሉ ናቸው ይላሉ የሕክምና ባለሙያው።
ጉበትን በቀላል እና ጤናማ በሆኑ ልምዶች እንዴት ማበረታታት ይቻላል?
• በየዕለቱ በቂ ንጹህ ውኃ በመጠጣት፤
• ጤናማ አመጋገብ በመከተል (እንደ ፍራፍሬ፣ አትክልት፣ ጤፍ፣ ባቄላ እና ዓሣ በመመገብ)፤
• ከመጠን በላይ ስብን እና ስኳርን በመቀነስ፤
• አካላዊ እንቅስቃሴን በማዘውተር፤
• አልኮልን በመገደብ ወይም በጭራሽ ባለመጠቀም፤
• የሄፓታይተስ ክትባት በመውሰድ፤
• ያልተረጋገጡ እፅዋትን ከመጠቀም በመቆጠብ፤
• መድኃኒት ከመውሰድ በፊት የጤና ባለሙያ በማማከር እንዲሁም የግል እና የምግብ ንጽህናን በመጠበቅ የጉበትን ጤንነት መጠበቅ ይቻላል ብለዋል ዶክተር አብዲ።
ሕክምናውን በተመለከተ
o ዶክተር አብዲ እንዳሉት፤ አብዛኛዎቹ የጉበት በሽታዎች ሊታከሙ ይችላሉ፤ በጊዜ ከተደረሰም መቆጣጠር እና መዳን ይችላሉ።
o ለሄፓታይተስ ቢ/ሲ ፀረ-ቫይረስ መድኃኒቶች ሕክምና መከታተል፤
o አልኮል መጠጣት በማቆም ጉበት በፍጥነት እንዲያገግም ማገዝ፤
o ለሰባ ጉበት፣ ለስኳር በሽታ እና ለኮሌስትሮል መብዛት በመድኃኒት ማከም፤
o አመጋገብን ማስተካከል፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ፤
o የከፋ ደረጃ ላይ የደረሰ ከሆነ እንደደረጃው የተለያዩ ሕክምናዎች መኖራቸውን ጠቅሰው፤ እስከ ንቅለ ተከላ ድረስ ሊታከም ይችላል ብለዋል።
ጉበት በዓለም አቀፍ ደረጃ….
👉 በዓለም አቀፍ ደረጃ ወደ 2 ቢሊየን የሚጠጉ ሰዎች እንደ ሄፓታይተስ ቢ እና ሲ ያሉ የጉበት ህመሞች ተጋላጭ ናቸው።
ለዚህም ከመጠን በላይ አልኮል መጠጣት፣ ውፍረት እና የስኳር በሽታ በሰፊው በዓለም አቀፍ ደረጃ ብዙዎችን ተጋላጭ ያደርጋሉ ነው ያሉት።
👉 በአፍሪካ ውስጥ ወደ 80 ሚሊየን የሚጠጉ ሰዎች ለሄፓታይተስ ቢ በሽታ ተጋላጭነት ውስጥ ይኖራሉ።
ከዚህ ውስጥ 60 በመቶው የሚሆነው በክትባት ውስንነት፣ በጤና አጠባበቅ ተደራሽነት እና በአፍላቶክሲን የተበከሉ (እንደ በቆሎ እና ማሽላ ባሉ) ሰብሎች ምክንያት ለአደጋ ተጋላጭ ነው ብለዋል።
👉 በኢትዮጵያም እስከ 7 በመቶ ያህሉ ሕዝብ ለሄፓታይተስ ቢ ተጋላጭ መሆኑን ነው ያመላከቱት።
ለዚህም አልኮል አላግባብ መጠቀም፣ ጫት መጠቀም እና የስኳር በሽታ መጨመር ለብዙዎች በተለይም ከ40 ዓመት በላይ ለሆኑ ወንዶች ተጋላጭነትን እንደሚጨምር አስገንዝበዋል።
👉 በአጠቃላይ ክትባት በመውሰድ፣ ጤናማ የአኗኗር ዘይቤ በመከተል፣ ጤናማ አመጋገብ በማዘውተር ብሎም በወቅቱ በመታከም ተጋላጭነትን በመቀነስ የጉበት ጤንነትን መጠበቅ ይገባል ሲሉ መክረዋል።