የጤና አገልግሎት ስርዓቱን ሙሉ ለሙሉ በዲጂታል ሥርዓት እንዲመራ የሚያስችል ተግባር እየተከናወነ ነው

አዲስ አበባ፤ነሐሴ 26/2017 (ኢዜአ)፡-የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የጤና አገልግሎት ስርዓቱን ሙሉ ለሙሉ በዲጂታል ሥርዓት እንዲመራ የሚያስችል ተግባር እያከናወነ መሆኑን ገለጸ።

በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ በባዮ ቴክኖሎጂ ኢንስቲቱዩት እና በአፍሪካ ሲዲሲ ትብብር አለም አቀፍ የ "አሚክስ" ቴክኖሎጅ (AMICS) ኮንፈረንስ ዛሬ ተካሒዷል።

በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ  ሚኒስቴር የሚኒስትሩ የቴክኖሎጂ አማካሪ ስሜነው ቀስቅስ (ዶ/ር) በወቅቱ፤ "አሚክስ" (AMICS) ማለት የሴሎችና የፕሮቲኖች ቅንጣቶች ናቸው ብለዋል፡፡

የ"አሜክስ" ቴክኖሎጂ ማለት ደግሞ እነዚህን የሴሎችንና የፕሮቲኖች ቅንጣቶችን ለመመርመር የሚረዳ መሳሪያ መሆኑን አመላክተዋል፡፡

መንግስት ባለፉት ዓመታት ቴክኖሎጂን ማዕከል ያደረጉ በርካታ ስራዎችን በመስራቱ በሁለንተናዊ ዘርፎች አመርቂ ውጤቶችን ማስመዝገብ መቻሉን ተናግረዋል፡፡

በዛሬው ዕለትም በተለይ የጤናው አገልግሎት ዘርፉን ከፍ ወዳለ ምዕራፍ በሚያሸጋግር በ"አሜክስ" ቴክኖሎጂ ጉዳይ ላይ ውይይት መደረጉን ገልጸዋል።

አሜክስ ቴክኖሎጂ የህክምና አይነት ሲሆን የዘረመል ምርመራዎችን ጨምሮ ክትባቶችንና ሌሎች መድሃኒቶችን በአገር ውስጥ እንዲካሔዱና እንዲመረቱ የሚያስችል ነው ብለዋል።

ሰዎች በሚታመሙበት ወቅት የሰውነት ንጥረ ነገሮቻቸውን መርምሮ ትክክለኛ መድሃኒት በትክክለኛ ወቅት ለማሰጠት እንደሚያግዝም እንዲሁ፡፡

ይህ ቴክኖሎጂ ወደ ኢትዮጵያ ከገባ የጤናውን ዘርፍ አገልግሎት እንደሚያልቀው ጠቁመው፣ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ቴክኖሎጂው እንዲገባ ከአለም አቀፍ ተመራማሪዎች ጋር በትብብር እንደሚሰራ ነው የተናገሩት።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ምክትል ፕሬዚዳንት ጄይሉ ኡመር (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የኮንፈረንሱ ዋና አላማ ዜጎች አለም የደረሰበትን የህክምና ቴክኖሎጂ እንዲጠቀሙ ለማድረግ ነው ብለዋል፡፡

አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ "የአሚክስ" ቴክኖሎጂ ወደ ኢትዮጵያ ገብቶ አገልግሎት መስጠት እንዲጀምር በእውቀት ሽግግርም ሆነ በሌሎች ጉዳዮች ላይ የድርሻውን ለማበርከት ዝግጁ መሆኑን አመላክተዋል፡፡

በአዲስ አበባ ዪኒቨርሲቲ የጤና ሳይንስ ኮሌጅ በባዮ ኬሚስትሪ ዲፓርትመንት የባዮ ኬሚስትሪ ተባባሪ ፕሮፌሰር ሰለሞን ተበጅ በበኩላቸው፤ የአሚክስ ቴክኖሎጂው የጤና አገልግሎት ስርዓቱን የሚያልቅ ነው ብለዋል፡፡

ቴክኖሎጂው አካባቢን ቀድሞ በማወቅ ክትባቶችን ለማዘጋጅትና መዳህኒቶችን ለማምረት እንደሚረዳ ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ በጤናው ዘርፍ እያከናወነቻቸው ያሉ ተግባራት ተሞክሮ የሚወሰድባቸው መሆናቸውን የተናገሩት ደግሞ በጃፓን ሆካዶ የኒቨርሲቲ ተባባሪ ፕሮፌሰር ሲዳባሳቭ ጎወአ ናቸው፡፡

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም