ለሕዳሴው ግድብ የተደረገውን ድጋፍ ማስቀጠል ከተቻለ ተጨማሪ የልማት ድል ማስመዝገብ ይቻላል - ኢዜአ አማርኛ
ለሕዳሴው ግድብ የተደረገውን ድጋፍ ማስቀጠል ከተቻለ ተጨማሪ የልማት ድል ማስመዝገብ ይቻላል
ወላይታ ሶዶ/ቦንጋ፤ነሐሴ 26/2017(ኢዜአ)፦ለሕዳሴው ግድብ ያለልዩነትና ስስት የተደረገውን ድጋፍ ማስቀጠል ከተቻለ ተጨማሪ የልማት ድል ማስመዝገብና የብልጽግና ተምሳሌት መሆን ይቻላል ሲሉ የወላይታ ሶዶ እና የቦንጋ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ።
የኢትዮጵያዊያን የአብሮነት፣የአይበገሬነትና የጥንካሬ ማሳያ የሆነውን ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ገድብን በማስመልከት ኢዜአ በወላይታ ሶዶ እና በቦንጋ ከተሞች ነዋሪዎችን አነጋግሯል።
የሕዳሴው ግድብ ለምረቃ በመብቃቱ ድስታና ኩራት እንደሚሰማቸው የገለጹት ነዋሪዎቹ፣ ግድቡ የኢትዮጵያዊያን የአብሮነትና የአንድነት ቃል ኪዳን ሆኖ በደማቅ ታሪክ እንደሚጻፍም ተናግረዋል።
የሕዳሴውን ግድብ በመተባበር እውን ማድረግ እንደተቻለ ሁሉ ያለልዩነትና ያለስስት ድጋፍን ማስቀጠል ከተቻለ ተጨማሪ የልማት ፕሮጀክቶችን በማሳካት የተጀመረውን ሀገራዊ የብልጽግና ጉዞ ማፋጠን እንደሚቻልም ገልጸዋል።
አስተያየታቸውን ከሰጡት የወላይታ ሶዶ ከተማ ነዋሪዎች መካከል አቶ ይልማ ኢልካ እንዳሉት፥ የግድቡ ግንባታ እውን እስኪሆን ድረስ ቦንድ በመግዛትና ሌሎችንም በማስተባበር ሲደግፉ ቆይተዋል።
የሕዳሴው ግድብ ሁሉንም ኢትዮጵያውያን ከዳር እስከ ዳር አነቃንቆ ለልማት በአብሮነት ከማቆም ባለፈ በትብብር ሌላ ተጨማሪ የልማት ድል ማሳካት እንደሚንችል በተጨባጭ ያሳየ ነው ብለዋል።
"ለትውልዱ የኩራትና የልማት ተስፋ የሆነው የሕዳሴው ግድብን ለማጠናቀቅ ያለስስትና ያለልዩነት የተደረገውን ድጋፍ ማስቀጠል ከተቻለ ሌሎች ልማቶችንም በማሳካት ኢትዮጵያን የብልጽግና ተምሳሌት ማድረግ ይቻላል" ሲሉም አቶ ይልማ ተናግረዋል።
የሕዳሴው ግድብ ህዝብን ለልማት በአንድነት ያሰለፈ፣ የጀግንነትና የሉአላዊነት መገለጫችን ነው ያሉት ደግሞ የወላይታ ሶዶ ከተማ ነዋሪ አቶ ታምራት ዎጋሶ ናቸው።
ባለፉት ዓመታት ከደመወዛቸው ተቆራጭ አድርገው ድጋፍ ሲያደርጉለት የነበረው የሕዳሴው ግድብ ዛሬ ላይ ለፍሬ በመብቃቱ መደሰታቸውን ገልጸዋል።
ግድቡ ኢትዮጵያ የጀመረችውን የከፍታ ጉዞ ለዓለም ከማሳየት ባለፈ በሁሉም ኢትዮጵያዊያን ዘንድ የእኔነት ስሜት ፈጥሯል፤ የአብሮነትና እና የጥንካሬያችን መገለጫ ነው ሲሉም ተናግረዋል።
የሕዳሴው ግድብ በበርካታ ጫናዎችና ፈተናዎች ውስጥ አልፎ በኢትዮጵያዊያንና በመንግስት የተባበረ ክንድ ለምረቃ መብቃቱን የገለጸው ደግሞ የቦንጋ ከተማ ነዋሪ ወጣት ታምራት ሀይሌ ነው።
ከልጅ እስከ አዋቂ በአንድነት ያቆመ የዘመናችን አድዋ ነው ያለው ወጣቱ፣ ግድቡ በትብብር ከተሰራ የማይቻል ፕሮጀክት እንደማይኖርና የአንድነት ማሳያ መሆኑን ተናግሯል።
በመሆኑም በሕዳሴው ግድብ ያሳየነው ትብብርና አብሮነት በሌሎች የልማት ፕሮጀክቶች መድገም ይገባናል ብሏል።
የሕዳሴው ግድብ ግንባታ ከተጀመረ አንስቶ ቦንድ በመግዛትና በሀሳብ ጭምር ድጋፍ ሲያደርጉ እንደነበር የገለጹት ሌላኛው የቦንጋ ከተማ ነዋሪ አቶ ታመነ በየነ፣ ግድቡ ተጠናቆ ሲመረቅ ከማየት በላይ ደስታ የለም ብለዋል።
"ግድቡ የተለያየ አስተሳስብ ያላቸውን ያስታረቀ የቃልኪዳን ውላችን ነው" ያሉት አቶ ታመነ በኢትዮጵያውያን ላይ የይቻላል መንፈስን ያሰረጸ ታላቅ ፕሮጀክት መሆኑንም ተናግረዋል።
በራስ አቅም ትልልቅ ፕሮጀክቶችን ማሳካት እንደምንችል ያሳየነውን አቅምበሌሎች የልማት ሥራዎች በመድገም የምንመኛትን የለማች ሀገር ለልጆቻችን እናውርስ ሲሉም ገልጸዋል።