የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማሕበር ድጋፍ ለሚሹ ወገኖች ፈጥኖ በመድረስ እያደረገ ያለው እገዛ የሚበረታታ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማሕበር ድጋፍ ለሚሹ ወገኖች ፈጥኖ በመድረስ እያደረገ ያለው እገዛ የሚበረታታ ነው
ገንዳ ውሃ፤ ነሐሴ 26/2017(ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማሕበር በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ችግር ድጋፍ ለሚሹ ወገኖች ፈጥኖ በመድረስ እያደረገ ያለው እገዛ የሚበረታታ መሆኑ ተገለጸ።
የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማሕበር በምዕራብ ጎንደር ዞን እያከናወናቸው ባሉ ሰብአዊ ድጋፍና አገልግሎቶች ዙሪያ ለሚዲያና ኮሙኒኬሽን ባለሙያዎች የግንዛቤ ማስጨበጫያ መድረክ ተካሄዷል።
በመድረኩ ላይ የተገኙት የምዕራብ ጎንደር ዞን ጤና መምሪያ ተወካይ ኃላፊ አቶ አጥቃው ተዋበ እንዳመለከቱት፤ ማሕበሩ መንግስት የሕብረተሰቡን ጤና ለመጠበቅ እያደረገ ያለውን እንቅስቃሴ በመደገፍ የድርሻውን እየተወጣ ነው።
ማሕበሩ እያደረጋቸው ያሉት ሌሎችንም ሰብአዊ ድጋፎች ለውጥ እንዲያመጡ መረጃ ተደራሽ በማድረግ በኩል የሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ባለሙያዎች የድርሻቸውን ሊወጡ ይገባል ብለዋል።
ሌላኛው የመድረኩ ተሳታፊ አቶ ታረቃኝ ንጋቱ በበኩላቸው እንዳሉት፤ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማሕበር በአካባቢው በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ችግር ድጋፍ ለሚሹ ወገኖች ፈጥኖ በመድረስ እያደረገ ያለው ድጋፍ የሚበረታታ ነው።
ቀጣይ የማሕበሩን ሰብአዊ ድጋፍና አገልግሎቶች በሕብረተሰቡ ተሳትፎ ጭምር ይበልጥ ተጠናክሮ እንዲቀጥል በማስተማርና መረጃን ተደራሽ በማድረግ የበኩላቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማሕበር የአካባቢው ጽሕፈት ቤት የፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ ሙላው አምዴ እንደገለጹት፤ በዞኑ የሱዳን ስደተኞችን ጨምሮ የአካባቢውን ማሕበረሰብ በመደገፍ ሰብዓዊ ተግባራት እየተከናወኑ ነው።
የዕለት ምግብና ውሃ፣ የውኃ ተቋማትን መጠገንና መገንባትን ጨምሮ ሌሎችንም ድጋፎችን እያደረገን ነው ያሉት አስተባባሪው፤ የሚዲያና የኮሙዩኒኬሽን ባለሙያዎች ይሕንን ተገንዝበው በሙያቸው መደገፍ እንዳለባቸው አመልክተዋል።
በመድረኩ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ባለሙያዎች፣ የጤና ባለሙያዎችና በጎ ፈቃደኞች ተሳትፈዋል።