የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ተቀናጅቶ መሥራት የህዝብን ተጠቃሚነት ለማሳደግ ጉልህ ሚና አለው - ኢዜአ አማርኛ
የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ተቀናጅቶ መሥራት የህዝብን ተጠቃሚነት ለማሳደግ ጉልህ ሚና አለው
ሠመራ፤ ነሐሴ 26/2017 (ኢዜአ)፡-የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ተቀናጅቶ መሥራት የህዝብን ተጠቃሚነት ለማሳደግ ጉልህ ሚና እንዳለው ተመለከተ።
በአፋር ክልል የሚገኙ ስምንት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች "ዳጉ ኢትዮጵያን ዴቭሎፕመንት ኮንሰርቲየም" በሚል ስያሜ በዛሬው ዕለት ጥምረት ፈፅመዋል።
በዕለቱ የተገኙት የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበራት ድርጅቶች ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ተወካይ አቶ መስፍን ተክለአብ እንደተናገሩት ዛሬ በራስ ተነሳሽነት የተደረገው የድርጅቶቹ ጥምረት በእጅጉ የሚደነቅ ነው።
ለጥምረቱ ዕውን መሆን የአቅም ግንባታ፣ የማበረታቻና የቴክኒክ ድጋፍ ስራዎች በምክር ቤታቸው በኩል መደረጉን ጠቅሰው ይህም በሌሎች አካባቢዎችም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።
የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ፎረም ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ጌትነት ካባ በበኩላቸው ድርጅቶቹ መጣመራቸው የህብረተሰቡን ዘላቂ ልማትና ሁሉን አቀፍ ሥራዎችን ለማቀላጠፍ ያግዛል።
ጥምረቱ በህብረተሰቡ ውስጥ አገልግሎት ከመሥጠት ባሻገር እንደ ጤና፣ ትምህርት እና ግብርና ዘርፍ ያሉ ማህበራዊ ተግዳሮቶችን ለመፍታት የበኩሉን እንደሚወጣም ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር ፅህፈት ቤት ምክትል ኀላፊ አቶ ኑር ጣሂር እንደተናገሩት ድርጅቶቹ ተጣምረው መሥራታቸው የህዝብን ተጠቃሚነት ለማሳደግ የሚያስችል ነው።
ጥምረቱ የክልሉን ነባራዊ ሁኔታ በመረዳት ተጨባጭ የለውጥ ሥራዎችን ለማስመዝገብ የሚያስችል መሆኑንም ገልፀዋል።
የክልሉ መንግስትም ለጥምረቱ መጎልበት አስፈላጊውን ድጋፍና ትብብር ያደርጋል ያሉት አቶ ኑር፣ ድርጅቶቹ ለህዝቡ ተጠቃሚነትና ለሀገር እድገት የድርሻቸውን ሊወጡ ይገባል ብለዋል።