በክልሉ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ በቦንድ ግዢ ከ291 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ተደርጓል - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ በቦንድ ግዢ ከ291 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ተደርጓል
ዲላ ፤ ነሐሴ 26/2017 (ኢዜአ)፡- በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ በቦንድ ግዢ ከ291 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ መደረጉን የክልሉ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ምክር ቤት ገለጸ።
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የክልሉ ህዝብ በቦንድ ግዢ ከ291 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ያደረገ ሲሆን የህዳሴው ግድብ ለፍጻሜ መብቃቱም ህዝባዊ ተሳትፎው ፍሬ ማፍራቱን የሚያሳይ እንደሆነም ተገልጿል።
የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳደርና የህዳሴው ግድብ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ምክር ቤት ሰብሳቢ አበባየሁ ታደሰ (ዶ/ር) ግድቡ ለፍጻሜ መብቃቱን ተከትሎ ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል።
ስብሳቢው በቆይታቸው እንዳሉት በለውጡ መንግስት ቆራጥ አመራርና በነቃ የህዝብ ተሳትፎ የህዳሴውን ግድብ እውን ማድረግ ተችሏል።
በዚህም ልክ እንደሌሎቹ የሃገራችን ህዝቦች ሁሉ የክልሉ ህዝብ ግድቡ ለፍጻሜ በቅቶ ትውልዱ የራሱን ታሪክ እንዲሰራ አሻራውን አሳርፏል ብለዋል።
የግድብ ግንባታው መጠናቀቅ ያለምንም የውጭ ብድርና እርዳታ በውስጥ አቅም ብቻ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን ማከናወን እንደሚቻል ትምህርት የሰጠ ነው ብለዋል።
የክልሉ ህዝብ ለግድቡ መጠናቀቅ ቦንድ በመግዛት፣ የሃብት ማሰባሰብ ስራዎችን በማስተባበርና በሌሎችም ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን አንስተው በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ብቻ በቦንድ ግዢ ከ291 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ማድረጉን ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅት የግድቡ ለፍጻሜ መብቃት ህዝባዊ ተሳትፎው ፍሬ ማፍራቱን የሚያሳይ ነው ያሉት ሰብሳቢው ከሃገር አልፎ በታችኛው የወንዙ ተፋሰስ ሀገራት የእኩል ተጠቃሚነትን በማረጋገጥ ረገድም ሚናው የጎላ ነው ብለዋል።
እንደ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሁሉ በሌሎች የልማት ፕሮጀክቶችና የባህር በርን በህጋዊና በሰላማዊ መንገድ የማግኘት መብትን ማስከበር ላይ እየታየ ያለው ህዝባዊ ተሳትፎ መጠናከር እንዳለበትም ተናግረዋል።