የሰላም ሰራዊት አባላት የከተማዋ ሰላም በማንኛውም እኩይ ተግባር የማይደፈርስ እንዲሆን አስችለዋል - ከንቲባ አዳነች አቤቤ - ኢዜአ አማርኛ
የሰላም ሰራዊት አባላት የከተማዋ ሰላም በማንኛውም እኩይ ተግባር የማይደፈርስ እንዲሆን አስችለዋል - ከንቲባ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 26/2017 (ኢዜአ)፡- የሰላም ሰራዊት አባላት ከመላው የጸጥታ መዋቅር ጋር በመሆን የከተማዋ ሰላም በማንኛውም እኩይ ተግባር የማይደፈርስ እንዲሆን ማስቻላቸውን የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።
የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ በንድፈ ሀሳብና በተግባር ያሰለጠናቸውን የሰላም ሰራዊት አባላት አስመርቋል።
የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በወቅቱ እንደገለጹት፤ ሰላምን መጠበቅና ማጽናት የሁሉም ዜጋ ሀላፊነት ነው።
የሰላም ሰራዊት አደረጃጀት ውጤታማ የሆነ የሰላም እሴት ግንባታ እንዲፈጠር ማስቻሉን ጠቁመዋል።
የሰላም ሰራዊት አባላት ከመላው የጸጥታ መዋቅር ጋር በመሆን የከተማዋ ሰላም በማንኛውም እኩይ ተግባር የማይደፈርስ እንዲሆን ማስቻላቸውን አንስተዋል።
የሰላም ሰራዊት አባላት ከጸጥታ አካላት ጋር ያከናወኑት ስራ ውጤታማ መሆኑን ገልጸው፤ ይህንን ስራ ይበልጥ ማጠናከር እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የሰላም ሰራዊት አባላት በመዲናዋ ዘላቂ ሰላም እንዲረጋገጥና ልማት እንዲፋጠን ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከቱ መሆኑንም ተናግረዋል።
ተመራቂዎች የተጣለባቸውን ሃላፊነት በመገንዘብ ለመዲናዋ ሰላም በቁርጠኝነት እንዲሰሩም የስራ መመሪያ ሰጥተዋል።
ስራቸውንም ያለምንም አድልኦ በታማኝነት መወጣት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
ከጸጥታ አካላት ጋር በቅርበት በመስራት የህዝቡን የሰላም እሴት ማዳበር ላይ በትኩረት መስራት እንዳለባቸው አመላክተዋል።
የአዲስ አበባ ሰላም እና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ ሀላፊ ሊዲያ ግርማ በበኩላቸው፤ ተመራቂዎች የንድፈ ሀሳብ እና የተግባር ስልጠናን ያጠናቀቁ መሆናቸውን ገልጸዋል።
የሰላም ሰራዊት በከተማው የማያቋርጥ ልማት እንዲሳለጥ እንዲሁም አስተማማኝ ሰላም እንዲኖር ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑንም ተናግረዋል።
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከመላው የጸጥታ መዋቅር ጋር በመተባበር ውጤታማ ስራ መሰራቱን ጠቁመዋል።
የሰላም ሰራዊት ህዝቡ የሰላም ባለቤት እንዲሆን በማድረግ በኩልም ጉልህ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ተናግረዋል።
በቀጣዮቹ ጊዜያትም በመዲናዋ በርካታ ዓለም አቀፍ እና ሀገር አቀፍ ሁነቶች እንደሚካሄዱ ገልጸዋል።
የሰላም ሰራዊት አባላት ከሌሎች የጸጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት ሁነቶች በስኬት እንዲጠናቀቁ በጋራ እንደሚሰሩ አመልክተዋል።
የሰላም ሰራዊት የከተማዋ ኩራት የሆነ የጸጥታ አደረጃጀት መሆኑን ጠቁመዋል።
ከተመራቂዎች መካከል መስፍን አዱኛ እና ፊራኦል ደበላ በስልጠናው ባገኙት እውቀት መሰረት የተጣለባቸውን ሀላፊነት እንደሚወጡ አረጋግጠዋል።
ከጸጥታ አካላት ጋር በጋራ በመሆን የከተማዋን ሰላም ይበልጥ አስተማማኝ ለማድረግ እንደሚሰሩ ተናግረዋል።
በቀጣይ በመዲናዋ የሚከናወኑ ጉባኤዎች እና በዓላት በስኬት እንዲጠናቀቁ የሚጠበቅባቸውን ሚና እንደሚወጡ ገልጸዋል።