የነብዩ ሙሀመድን ልደት ስናከብር የሰላምና የአብሮነት እሴቶችን ማሰብ ይገባል - የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት - ኢዜአ አማርኛ
የነብዩ ሙሀመድን ልደት ስናከብር የሰላምና የአብሮነት እሴቶችን ማሰብ ይገባል - የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 26/2017 (ኢዜአ)፡-የነብዩ ሙሀመድ የልደት በዓል ሲከበር የሰላምና የአብሮነት እሴቶችን በማስታወስ ሊሆን እንደሚገባ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ገለጸ፡፡
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የፊታችን ሀሙስ ነሐሴ 29 ቀን 2017 ዓ.ም በታላቁ አንዋር መስጂድ የሚከበረውን 1 ሺህ 500ኛውን የነቢዩ ሙሀመድ የልደት በዓል በተመለከተ ለመገናኛ ብዙኅን መግለጫ ሰጥቷል፡፡
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የወጣቶችና ሴቶች ዘርፍ ተጠሪና የስራ አስፈጻሚ አባል ሸህ አብዱል ሃሚድ አህመድ እንዳሉት፤ የታላቁ ነቢይ አስተምህሮ የመከባበር፣ መግባባት እና በሰላም አብሮ የመኖር መሰረት መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በመሆኑም ህዝበ ሙስሊሙ ከሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር በመተባበር የመቻቻልና የመከባበር እሴቶችን አጠናክሮ ማስቀጠል ይጠበቅበታል ብለዋል፡፡
የነብዩ ሙሀመድን ልደት ስናከብር የሰላም፣ መቻቻል እና ከሌሎች ጋር ተከባብሮ በአንድነት የመኖር እሴቶችን በማጎልበት ሊሆን ይገባል ሲሉም አሳስበዋል፡፡