በጋራ ትርክት ግንባታ፣ በሰላምና በልማት አጀንዳዎች ላይ በቅንጅት የተሰራው ሥራ ተጨባጭ ውጤት እያመጣ ነው- ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ - ኢዜአ አማርኛ
በጋራ ትርክት ግንባታ፣ በሰላምና በልማት አጀንዳዎች ላይ በቅንጅት የተሰራው ሥራ ተጨባጭ ውጤት እያመጣ ነው- ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ

ሀዋሳ ፤ ነሐሴ 26/2017 (ኢዜአ)፡-በሲዳማ ክልል በጋራ ትርክት ግንባታ፣ በሰላምና በልማት አጀንዳዎች ላይ በቅንጅት የተሰራው ሥራ ተጨባጭ ውጤት እያመጣ መሆኑን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ ገለጹ።
የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ደስታ ሌዳሞ፤ በክልሉ ባለፉት ዓመታት በሁሉም ዘርፎች የተከናወኑ ዋና ዋና ሥራዎችና የመጡ ውጤቶችን በተመለከተ ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል።
ከዘላቂ ሰላም ግንባታና የልማት ሥራዎችን ውጤታማ ከማድረግ አንፃር ብዙ ተሰርቶ ውጤቶችም መመዝገባቸውን ያነሱት ርዕሰ መስተዳድሩ ውጤቶቹም የህዝብ እገዛና የመንግስት ጥረት ታክሎበት የመጡ መሆናቸውን ገልጸዋል።
የክልሉ ህዝብና መንግስት ለጋራ ትርክት ግንባታ፣ ለሰላምና የልማት አጀንዳዎች መሳካት በቅርበትና በትብብር መስራታቸው የሚፈለገውን ውጤት ለማምጣት አግዟል ብለዋል።
በክልሉ ያለውን እምቅ ሃብት በማልማት የመጠቀም ጥረት፣ ለሰላምና የልማት አጀንዳዎች በጋራ በመትጋት በተለይም በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ስኬት መመዝገቡን ለአብነት አንስተዋል።
በፖለቲካው፣ በማህበራዊ ዘርፍና በምጣኔ ሃብት እድገት ረገድም በመንግስት የተያዙ ኢኒሼቲቮችን በመተግበርና ውጤታቸውን በመገምገም ድክመቶችን በማረም፤ ስኬቶችን ደግሞ አጠናክሮ በማስቀጠል ላይ እንገኛለን ሲሉም አረጋግጠዋል።
የብልጽግናን ግብ ለማሳካት የህዝቡን ኢኮኖሚያዊ አቅም መገንባት ያስፈልጋል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፣ ያሉ አቅሞች ተለይተው ወደ ሥራ መገባቱን ጠቁመዋል።
በክልሉ የግብርና ምርታማነትን በማሳደግ፣ የቱሪዝም መስህብ ስፍራዎችን በማስፋትና ለጎብኚዎች ምቹ በማድረግ፣ በገጠርና በከተሞች የኮሪደር ልማት፣ በኢንቨስትመንት እንዲሁም በሌማት ትሩፋት የሚታይ ተጨባጭ ለውጥና ውጤትም መምጣቱንም አብራርተዋል።
የሲዳማ ክልል በሁሉም ዘርፍ ዕምቅ ጸጋ እንዳለው ያነሱት አቶ ደስታ ለዘላቂ ሰላምና ልማት የጋራ አቋም በመያዝ፣ የጋራ ትርክት በመገንባትና ህብረ ብሔራዊ አንድነትን በማፅናት ለኢትዮጵያ ማንሰራራት እንሰራለን ብለዋል።
የተሻለ የጤና አገልግሎት፣ የመሰረተ ልማት፣ የትምህርት ጥራትና ተደራሽነትን በማስፋፋት ለላቀ ስኬት ለመብቃት እንተጋለን ሲሉም አረጋግጠዋል።
በኢትዮጵያ የመጣውን ለውጥ ተከትሎ ለልማት አጀንዳዎች ትኩረት በመስጠት፣ ሰላምን በማጽናትና አሰባሳቢ ትርክትን በመገንባት ለጋራ የብልጽግና ስኬት መትጋት የሁላችንም የጋራ አጀንዳ ሆኖ መቀጠል አለበት ሲሉም ተናግረዋል።