ብልጽግና ፓርቲ በሀገሪቱ የብልጽግና ጉዞን ለማሳካት ባከናወናቸው ተግባራት ስኬት እያስመዘገበ  ነው

ሀዋሳ ፤ ነሐሴ 26/2017 (ኢዜአ)፡- ብልጽግና ፓርቲ ባለፉት ዓመታት በሀገሪቱ የብልጽግና ጉዞን ለማሳካት ባከናወናቸው ተግባራት ስኬት እያስመዘገበ  መሆኑን የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንትና በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማእረግ የዲሞክራሲ ስርአት ግንባታ ማስተባበሪያ ማእከል ሀላፊ አቶ አደም ፋራህ አስታወቁ። 

አቶ አደም ፋራህ  በሀዋሳ ከተማ አስተዳደር የዳካ ክፍለ ከተማ የፓርቲውን ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት መርቀው ስራ አስጀምረዋል። 


 

አቶ አደም በምረቃ ስነስርዓቱ ላይ  እንዳሉት ብልጽግና ፓርቲ ከተመሰረተበት ጊዜ አንስቶ ባሉት አመታት የህዝብንና የሀገሪቱን ብልጽግና ለማምጣት ያከናወናቸው ተግባራት ስኬታማ ናቸው። 

ለስኬቱ መላው አባሉና ደጋፊው ያለው ጥልቅ ፍቅር፣ የመደመር ፍልስፍናን ተከትሎ መስራት መቻሉ እና ለፓርቲው በትጋት ማገልገሉ እንደሆነ ተናግረዋል። 

የሲዳማ ህዝብ ለፓርቲው ባለው ዕምነትና ታማኝነት የሚወርዱ አቅጣጫዎችን በመቀበል በሌማት ትሩፋት መርሀ ግብር ባደረገው ተሳትፎ ስራውን በግንባር ቀደምነት በመስራት ለሌሎች ምሳሌ መሆን እንደቻለ ገልጸዋል። 


 

በሌሎች የልማት ስራዎችም በንቃት በመሳተፍ የድርሻውን እየተወጣ እንደሚገኝ ጠቁመው በኮሪደር ልማት  ስራ ሀዋሳ ባላት ውበት ላይ ተጨማሪ ውበት ያላበሰ ስራ መሰራቱን ጠቅሰዋል። 

የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ በበኩላቸው ህዝቡ ለክልሉ ልማት በገንዘብ፣ በጉልበትና በዕውቀት የሚጠበቅበትን እየተወጣ እንደሚገኝ ጠቁመዋል። 


 

ፓርቲው የተመቸ ተቋም እንዲኖረው በተቀመጠ አቅጣጫ መሰረት የአባላትና የደጋፊዎቹን  አቅም በመጠቀም ምቹ ጽህፈት ቤቶችን ገንብቶ ለአገልግሎት ማብቃቱን ተናግረዋል።

የፓርቲው የሲዳማ  ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሀላፊ አቶ አብርሀም ማርሻሎ እንዳሉት የተገነባው ባለ አራት ወለል ህንጻ ለስራ ምቹ ሁኔታን የፈጠረ ነው። 


 

በክልሉ ተግባራዊ በተደረገው የሌማት ትሩፋት መርሀ ግብር በርካቶች እየተለወጡ መሆኑንም ገልጸዋል። 

በምረቃ ስነስርዓቱ ላይ የብልጽግና ፓርቲ የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ኃላፊ ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር)፣ በብልጽግና ፓርቲ የዲሞክራሲ ባህል ግንባታ ዘርፍ ኃላፊ መለሰ ዓለሙን ጨምሮ ሌሎች የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም