የሰላም ሰራዊት አባላት በመዲናዋ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን እና ልማት እንዲፋጠን ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ነው - ከንቲባ አዳነች አቤቤ - ኢዜአ አማርኛ
የሰላም ሰራዊት አባላት በመዲናዋ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን እና ልማት እንዲፋጠን ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ነው - ከንቲባ አዳነች አቤቤ
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 26/2017 (ኢዜአ)፡- የሰላም ሰራዊት አባላት በመዲናዋ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን እና ልማት እንዲፋጠን ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከቱ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።
የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ በንድፈ ሀሳብና በተግባር ያሰለጠናቸውን የሰላም ሰራዊት አባላት አስመርቋል።
በመድረኩ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤን ጨምሮ የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች ተገኝተዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች በወቅቱ እንደገለጹት፤ ሰላምን መጠበቅና ማጽናት የሁሉም ዜጋ ሀላፊነት ነው።
የሰላም ሰራዊት አደረጃጀት ውጤታማ የሆነ የሰላም እሴት ግንባታ እንዲፈጠር ማስቻሉን ጠቁመዋል።
የሰላም ሰራዊት አባላት ከጸጥታ አካላት ጋር ያከናወኑት ስራ ውጤታማ መሆኑን ገልጸው፤ ይህንን ስራ ይበልጥ ማጠናከር እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የሰላም ሰራዊት አባላት በመዲናዋ ዘላቂ ሰላም እንዲረጋገጥና ልማት እንዲፋጠን ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከቱ መሆኑን ተናግረዋል።
ተመራቂዎች የተጣለባቸውን ሃላፊነት በመገንዘብ ለመዲናዋ ሰላም በቁርጠኝነት እንዲሰሩ የስራ መመሪያ ሰጥተዋል።
የአዲስ አበባ ሰላም እና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ ሀላፊ ሊዲያ ግርማ በበኩላቸው፤ ተመራቂዎች የንድፈ ሀሳብ እና የተግባር ስልጠናን ያጠናቀቁ መሆናቸውን ገልጸዋል።
የሰላም ሰራዊት በከተማው የማያቋርጥ ልማት እንዲሳለጥ እንዲሁም አስተማማኝ ሰላም እንዲኖር ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከቱ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከመላው የጸጥታ መዋቅር ጋር በመተባበር ውጤታማ ስራ መሰራቱን ጠቁመዋል።
የሰላም ሰራዊት ህዝቡ የሰላም ባለቤት እንዲሆን በማድረግ በኩልም ጉልህ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ተናግረዋል።
በቀጣዮቹ ጊዜያትም በመዲናዋ በርካታ ዓለም አቀፍ እና ሀገር አቀፍ ኹነቶች እንደሚካሄዱ ገልጸዋል።
የሰላም ሰራዊት አባላት ከሌሎች የጸጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት ኹነቶች በስኬት እንዲጠናቀቁ በጋራ እንደሚሰሩ አመልክተዋል።
የሰላም ሰራዊት የከተማዋ ኩራት የሆነ የጸጥታ አደረጃጀት መሆኑን ጠቁመዋል።