ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ኢትዮጵያ ወደ ብልፅግና የምታደርገውን ጉዞ ያፋጥናል -የግብርና ሚኒስትር አዲሱ አረጋ - ኢዜአ አማርኛ
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ኢትዮጵያ ወደ ብልፅግና የምታደርገውን ጉዞ ያፋጥናል -የግብርና ሚኒስትር አዲሱ አረጋ
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 26/2017 (ኢዜአ)፡- ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ኢትዮጵያ ወደ ብልፅግና የምታደርገውን ጉዞ ያፋጥናል ሲሉ የግብርና ሚኒስትር አዲሱ አረጋ ገለፁ።
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በህብረት እውን የሆነ የኢትዮጵያ የማንሰራራት ዘመን መገለጫ ብሎም የመቻል ማሣያ ነው፡፡
ይህ ግድብ በአንድነት ታሪክ መስራት እንደሚቻል የተረጋገጠበት የትውልድ ተሻጋሪ የልማት ትሩፋትም ነው።
ይህ ኢትዮጵያዊያን በራሳቸው የፋይናንስ አቅም የገነቡት ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ሊመረቅ ጥቂት ቀናት ብቻ ቀርተውታል።
ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የግብርና ሚኒስትር አዲሱ አረጋ ግድቡን በተመለከተ በሰጡት ማብራሪያ፤ ግድቡ የኢትዮጵያ የአንድነት አርማ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያውያን ካላቸው ላይ ቀንሰው በመስጠት ለሀገር ብልፅግና መረጋገጥ ያላቸውን ፅኑ አቋም ያሳዩበት እንደሆነም ተናግረዋል።
ኢትዮጵያዊያን በጋራ ከቆሙ ማንኛውንም ፈተና በማለፍ የጀመሩትን ስራ ማጠናቀቅ እንደሚችሉ ያረጋገጡበት ግድብም ነው ብለዋል።
የግድቡ መጠናቀቅ ለኢትዮጵያ በርካታ ጥቅሞች እንደሚያመጣ አንስተው፤ እንደአገር ሀይል የማመንጨት አቅምን ከፍ ያደርጋል ብለዋል።
ይህም የኤሌክትሪክ ሃይል ተደራሽነትን በማሳደግ ለአገር ኢኮኖሚ እድገት፣ ለኢንዱስትሪ መስፋፋት እና ግብርናን ለማሸጋገር ቁልፍ ሚና ይጫወታል ነው ያሉት።
በተጨማሪ ግድቡ ኢትዮጵያ የጀመረችውን የብልፅግና ጉዞ ያፋጥናል ሲሉም ሚኒስትሩ ገልፀዋል።
ግድቡ በአሳ ልማት ዘርፍ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንደሚሰጥ ጠቁመው፤ አሁን ላይም ወጣቶች በህብረት ስራ ማህበራት በመደራጀት የዓሳ ምርት ወደ ገበያ እያቀረቡ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የዓሳ ልማቱ ከወጣቶች የስራ ዕድል ፈጠራ ባሻገር በኢንዱስትሪ ደረጃ ዓሳን በማቀነባበር ለገበያ ማቅረብ የሚያስችል አቅም አለው ብለዋል።