ኢትዮጵያዊው ኢንተርናሽናል ዳኛ ባምላክ ተሰማ ራሱን ከዳኝነት አገለለ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያዊው ኢንተርናሽናል ዳኛ ባምላክ ተሰማ ራሱን ከዳኝነት አገለለ

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 26/2017 (ኢዜአ)፦ ኢንተርናሽናል ዳኛ ባምላክ ተሰማ ራሱን ከዳኝነት ዓለም ለማግለል መወሰኑን አስታውቋል።
ያለፉትን ረጅም ዓመታት በወጥነት በሀገር ውስጥ እና ዓለም አቀፍ መድረኮች በዳኝነት ያገለገለው ባምላክ ተሰማ ከዳኝነት ዓለም ራሱን ለማግለል መወሰኑን ለዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር(ፊፋ) በላከው መልዕክት ማሳወቁን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አመልክቷል።
በዓለም ዋንጫ፣ የአፍሪካ ዋንጫ፣ በከፍሪካ አገራት ሻምፒዮና (ቻን) ፣ ካፍ ቻምፒየንስ ሊግ፣ ኮንፌሬዴሽን ዋንጫ፣ የዓለም ክለቦች ዋንጫ እና ኦሊምፒክን ጨምሮ በርካታ ሀገራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ታላላቅ ጨዋታዎችን በመምራት የሀገሩን ስም ከፍ አድርጎ አስጠርቷል።
ባምላክ ኢትዮጵያን በሀገር አቀፍም ሆነ በዓለም አቀፍ መድረክ በማገልገሉ ኩራት እንደሚሰማው ገልጾ ፊፋ ለሰጠው ዕድል በማመስገን ከኢንተርናሽናል ዳኝነት ራሱን ማግለሉን አስታውቋል።
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ባምላክ ተሰማ በዳኝነት ዓለም ላሳለፈው ህይወት እና አበርክቶ ያለውን አድናቆት እና ምስጋናውን አቅርቧል።
በዳኝነት ለኢትዮጵያ ብሎም ለአፍሪካ ያበረከተው አስተዋፅኦ ሁሌም በኩራት የሚዘከር መሆኑን ፌዴሬሽኑ አመልክቷል።
ባምላክ በቀጣይ የህይወት ምዕራፉ መልካሙ ሁሉ እንዲገጥመውም ተመኝቷል።
የ45 ዓመቱ ባምላክ ተሰማ ከእ.አ.አ 2009 አንስቶ በፊፋ የኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ ሆኖ አገልግሏል።
ባምላክ ተሰማ ከእግር ኳስ ዳኝነት በተጨማሪ የነርሲንግ ሙያ ተመራቂ ሲሆን በሕክምና ሙያ በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኝ የጤና ተቋም ውስጥ በሙያው አገልግሏል።
ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሶሾሎጂ የመጀመሪያ ዲግሪውን አግኝቷል።
ባምላክ ተሰማ ገና በልጅነቱ በስነ ፈለክ(አስትሮኖሚ) እውቀቱና ሳይንሳዊ ትንታኔው ብዙዎችን ያስገረመው የሮቤል ባምላክ አባት ነው።