በተጠባቂው ጨዋታ ሊቨርፑል አርሰናልን አሸነፈ

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 25/2017(ኢዜአ)፦ በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የሶስተኛ ሳምንት ተጠባቂ መርሃ ግብር ሊቨርፑል አርሰናልን 1 ለ ዐ አሸንፏል።

ማምሻውን በአንፊልድ ሮድ ስታዲየም በተደረገው ጨዋታ የአማካይ ተጫዋቹ ዶምኒክ ስቦዝላይ በ83ኛው ደቂቃ ላይ ከረጅም ርቀት በግሩም ሁኔታ ያስቆጠረው ቅጣት ምት ለቀያዮቹ ወሳኝ ሶስት ነጥብ አስገኝታለች።

ሊቨርፑል በጨዋታው የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ቢወስድም የአርሰናልን ጠንካራ የተከላካይ መስመር ሰብሮ ለመግባት ሲቸገር ታይቷል።

አርሰናል በቆመ ኳስ እና በክንፍ ከሚሻገሩ ኳሶች ግብ ለማስቆጠር ያደረገው ጥረት ፍሬያማ አልነበረም።

የአርሰናል ተከላካይ ዊሊያም ሳሊባ በጨዋታው መጀመሪያ አካባቢ ባጋጠመው ጉዳት ተቀይሮ ገብቷል።

ውጤቱን ተከትሎ የወቅቱ የሊጉ አሸናፊ ሊቨርፑል በዘጠኝ ነጥብ የሊጉን መሪነት ከቼልሲ ተረክቧል።

በሊጉ የመጀመሪያ ሽንፈቱን ያስተናገደው አርሰናል በስድስት ነጥብ ወደ ሶስተኛ ደረጃ ዝቅ ብሏል።

ቀደም ብለው ዛሬ በተደረጉ ጨዋታዎች፤ ብራይተን ማንቼስተር ሲቲን 2 ለ 1 እንዲሁም ዌስትሃም ኖቲንግሃም ፎረስትን 3 ለ 0 አሸንፈዋል።

የዛሬው የጨዋታ መርሐ ግብር ሲቀጥል፤ ምሽት 3 ሠዓት ላይ አስቶንቪላ ከክሪስታል ፓላስ ይገናኛሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም