ቀጥታ፡

የአውሮፕላን ማረፊያ አገልግሎት መጀመር የልማት ስራዎችን ለማፋጠን ያስችላል - የቦረና ዞን ነዋሪዎች

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 25/ 2017(ኢዜአ)፡-የአውሮፕላን ማረፊያው አገልግሎት መጀመር አማራጭ የትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት የልማት ሥራዎችን ለማፋጠን እንደሚያስችል የቦረና ዞን ነዋሪዎች ገለጹ፡፡ 

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በኦሮሚያ ክልል ቦረና ዞን የያቤሎ አውሮፕላን ማረፊያን መርቀው ሥራ አስጀምረዋል።  


 

የያቤሎ አየር ማረፊያ አገልግሎት መጀመር የዘመናት የልማት ጥያቄ ምላሽ የሰጠ፤ የህዝቡንም ተጠቃሚነት በተግባር ያረጋገጠ መሆኑም ተጠቁሟል፡፡

የአውሮፕላን ማረፊያው ስራ መጀመር በቦረና የሚገኙ ውብ የታሪክና የተፈጥሮ ጸጋዎችን ለመግለጥ፣ የገበያ በሮችን እና የቱሪዝም መዳረሻ መንገዶችን ለመክፈት ትልቅ ዕድልን እንደሚፈጥር ተጠቅሷል፡፡

የቦረና ዞን ነዋሪዎች በሰጡት አስተያየትም የአውሮፕላን ማረፊያው ስራ መጀመር ለዘመናት የልማት ጥያቄዎቻቸው ተግባራዊ ምላሽ የሰጠ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

አቶ ዝናቡ ዓለሙ እንደገለጹት፤ የአውሮፕላን ማረፊያው ወደ አገልግሎት መግባት መንግስት ለአርብቶ አደሩ ማህበረሰብ የሰጠውን ትኩረት ያሳያል፡፡

የአርብቶ አደሩን ተጠቃሚነት በሁሉም ዘርፍ እንደሚያረጋግጥ ጠቁመው፤ በእንስሳት እና ሌሎች የንግድ ዘርፎች ያለውን ተሳትፎ ለማሳደግ እንደሚጠቅማቸውም ተናግረዋል፡፡

ብሩክታዊት ታደሰ በሰጠችው አስተያየት፤ የአየር መንገዱ ስራ መጀመር ለቱሪዝም እንቅስቃሴ መነቃቃት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ገልጻለች፡፡ 

በተለይም የሀገር ውስጥ እና የውጭ ጎብኚዎች የቦረና ብሔራዊ ፓርክን ጨምሮ ሌሎች የቱሪዝም መስህቦችን እንዲጎበኙ ዕድል የሚፈጥር መሆኑንም ተናግራለች፡፡

የአየር መንገዱን ስራ መጀመር በጉጉት እየተጠባበቁ እንደነበር ያስታወሱት ሌለኛው አስተያየት ሰጪ  ወይዘሮ ሽታዬ በየነ ዛሬ ደስታቸው እጥፍ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ 

የአውሮፕላን ማረፊያው ተገንብቶ አገልግሎት መጀመርም ከቦረና እስከ አዲስ አበባ በተሽከርካሪ ረጅም መንገድ ይጓዙ የነበረውን እንዳሳጠረው ጠቁመዋል፡፡

መንግስት ለህዝብ ጥያቄ ምላሽ እየሰጠ በመሆኑም መደሰታቸውን ተናግረዋል።

የያቤሎ አውሮፕላን ማረፊያ በአንድ ቢሊዮን ብር ወጪ የተገነባ ሲሆን፤ ግንባታው በአራት ዓመት መጠናቀቁ ተጠቁሟል።   

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም