በሁሉም መስክ የኢትዮጵያን የማንሰራራት ጉዞ የሚያበስሩ ተጨባጭ ስኬቶች አስመዝግበናል - ከንቲባ አዳነች አቤቤ - ኢዜአ አማርኛ
በሁሉም መስክ የኢትዮጵያን የማንሰራራት ጉዞ የሚያበስሩ ተጨባጭ ስኬቶች አስመዝግበናል - ከንቲባ አዳነች አቤቤ
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 25/2017 (ኢዜአ)፡-በሁሉም መስክ የኢትዮጵያን የማንሰራራት ጉዞ የሚያበስሩ ተጨባጭ ስኬቶች ማስመዝገብ መቻሉን የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።
የ'ለነገዋ የሴቶች ተሀድሶና ክህሎት ማበልፀጊያ ማዕከል በተለያየ የሙያ መስክ በ3ኛ ዙር ያሰለጠናቸውን 810 ሠልጣኖች አስመርቋል።
በሥነ-ስርዓቱ የተገኙት የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ÷ መንግስት የዜጎችን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ስኬታማ የልማት ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል ብለዋል።
የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ብልጽግና ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረትም ሴቶች ዕውቀትና ክህሎታቸውን በማዳበር እራሳቸውንና ሀገራቸውን የሚጠቅሙበት ምቹ መደላድል መፈጠሩን ገልጸዋል።
በተለይም ሴቶችን ለችግር የሚያጋልጡ መንስኤዎችን በመለየት ቀድሞ መከላከል የሚያስችል ስራ እየተሰራ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
ይሁኑ ታሳቢ በማድረግ የተገነባው የ'ለነገዋ የሴቶች ተሀድሶና ክህሎት ማበልፀጊያ ማዕከልም የሴቶችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያ ተጋላጭነት በማስቀረት የተሰጠውን ኃላፊነት በብቃት እየተወጣ ነው ብለዋል።
በዚህም በአስከፊ የኑሮ ሁኔታ ውስጥ የነበሩ ሴቶችን በዘላቂ የክህሎትና ሙያ ስልጠና በማብቃት ስኬታማ የህይወት መስመር የሚቀይሱበትን ወርቃማ እድል እያመቻቸ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
ማዕከሉ በሁለት ዙር ስልጠና ያሳለፋቸው ሴቶች ስኬታማ ህይወት እየመሩ ነው ያሉት ከንቲባ አዳነች÷ በ3ኛ ዙር የተመረቁ ሴቶችም በሙያቸው የሚሰማሩበት ዕድል መመቻቸቱን ለተመራቂዎቹ አብስረዋል።
ቀጣይ የሚፈጠርላቸውን መልካም አጋጣሚ በመጠቀም በሚሰማሩባቸው የሙያ መስኮች ሊያጋጥሟቸው የሚችሉ ውጣ ውረዶችን ወደ ዕድል በመቀየር ስኬታማ መሆን እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል።
ማዕከሉ ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር ተጋላጭ የሆኑ ሴቶችን በዕውቀትና ክህሎት በማብቃት ለሚያደረገው ጥረት ድጋፍ የሚያደርጉ ተባባሪ አካላትም ምስጋና አቅርበዋል።
ኢትዮጵያም በሁሉም መስክ የማንሰራራት ጉዞዋን የሚያበስሩ ተጨባጭ ስኬቶችን ማስመዝገብ እንደቻለች አስታውቀዋል።
ለአብነትም የታላቁ የሕዳሴ ግድብ መጠናቀቁን፣ በአረንጓዴ አሻራ፣ በስንዴ ምርታማነትና መሰል የልማት መስኮች ስኬት መመዝገባቸውን አስረድተዋል።
የኢትዮጵያን ክብር የሚመጥኑ ግዙፍ የልማት ስራዎች እየተሰሩ ነው ያሉት ከንቲባ አዳነች÷ የኢትዮጵያ ተስፋም የሚጨበጥ፣ የሚታይ እውነትና ማንሰራራት የሚናገሩ ስራዎች ውጤታማ ሆነዋል ብለዋል።
የ'ለነገዋ የሴቶች ተሀድሶና ክህሎት ማበልፀጊያ ማዕከል ዋና ዳይሬክተር ሔርጳሳ ጫላ (ዶ/ር)÷ በ3ኛ ዙር ስልጠና አጠቃላይ 810 ሠልጣኞች ለምርቃት መብቃታቸውን አስታውቀዋል።
በማዕከል እስካሁን የክህሎትና የሙያ ስልጠና የወሰዱ ሴቶች 1ሺህ 692 ሰልጣኞች ከነበሩበት አስከፊ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ህይወት በማላቀቅ የስራ ዕድል ተጠቃሚ አንዲሆኑ መደረጉን ገልጸዋል።
በማዕከሉ የክህሎትና የሙያ ስልጠና የሚያልፉ ሴቶችም ለቀጣይ ህይወታቸው ስንቅ የሚሆን የንድፈ ሃሳብና የተግባር ስልጠና ተከታትለው ወደስራ ዓለም አንዲቀላቀሉ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
በማዕከሉ የክህሎትና የሙያ ስልጠና ወስደው ከተመረቁት መካከል ወይንሸት ብርሃኑ ቀጣይ ህይወቷን በአረንጓዴ ልማት ዘርፍ በተሻለ መምራት የምትችልበትን ስኬታማ ስልጠና መውሰዷን ገልጻለች።
ሌላኛዋ የማዕከሉ ተመራቂ ሀሊማ የሱፍ÷ የነገ ህይወቷን በዶሮ እርባታ ዘርፍ በአዲስ ምዕራፍ የምትጀመርበትን ዕድል እንደተፈጠረላት ተናግራለች።
ሌላዋ ተመራቂ ቅድስት ታሪኩ በበኩሏ በቆይታዋ ለቀጣይ ህይወቷ ስንቅ የሚሆን የክህሎትና የሙያ እውቀት መቅሰሟን አንስታለች።