የያቤሎ አውሮፕላን ማረፊያ የህልሞቻችን ማሳኪያ መንገድ ጭምር ነው - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን - ኢዜአ አማርኛ
የያቤሎ አውሮፕላን ማረፊያ የህልሞቻችን ማሳኪያ መንገድ ጭምር ነው - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 25/2017 (ኢዜአ)፡- ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ የያቤሎ አውሮፕላን ማረፊያ ከኮንክሪት የተሠራ የአውሮፕላን ማረፊያና ማኮብኮቢያ ብቻ ሳይሆን የህልሞቻችን ማሳኪያ መንገድ ጭምር ነው ሲሉ ገለጹ።
ምክትል ጠቅይ ሚኒስትሩ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት ለቦረና ሕዝብ አዲስ የተስፋና የልማት መንገድ የሆነውን የያቤሎ አውሮፕላን ማረፊያ መርቀን ሥራ አስጀምረናል ብለዋል።
አውሮፕላን ማረፊያው የሕዝቡን የረጅም ጊዜ የልማት ጥያቄ የመለሰ፣ ታሪክና እሴትን ከነገ መዳረሻ፣ ቅርስን ከዕድገት፣ ሕዝብን ከልማት ጋር ያገናኘ አዲስ የግንኙነት እና የተስፋ አድማስን የከፈተ ነው ሲሉም ገልጸዋል።
የቦረና ሕዝብ የዳር ድንበራችን ዘብ፣ የጥንቱ የገዳ ስርዓት ጠባቂ፣ የሰላም፣ የሕግ እና የነፃነት አርዓያ ሆኖ ኖሯል ያሉት አቶ ተመስገን፤ አስከፊ ድርቅን በአስደናቂ የውሃ አጠባበቅ ጥበቡ በመሻገር የጽናት ማሳያም ጭምር ሆኗል ብለዋል።
ዛሬ የተመረቀው የአውሮፕላን ማረፊያ በቦረና የሚገኙ ውብ የታሪክና የተፈጥሮ ጸጋዎችን ለመግለጥ፣ የገበያ በሮችን እና የቱሪዝም መዳረሻ መንገዶችን ለመክፈት ትልቅ ዕድልን ይፈጥራል ሲሉም አስገንዝበዋል።
በተጨማሪም አየር መንገዳችን የሀገር ውስጥ የአየር ትራንስፖርትን በማስፋፋት የሕዝባችንን ትስስር እንዲያጠናክርና ለሁላችንም የምትመች ሀገር የመገንባት የጋራ ህልማችንን ያሳካል ብለዋል።
የቦረና ዞንና የያቤሎ ከተማ ሕዝብ፣ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር እና ከፍተኛ አመራሮች ላደረጉላቸው አቀባበል አመስግነው፤ የያቤሎ አውሮፕላን ማረፊያ ሥራ በመጀመሩ የቦረና እና አካባቢው ሕዝብ እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል።