የያቤሎ አየር ማረፊያ አገልግሎት መጀመር የዘመናት የልማት ጥያቄ ምላሽ የሰጠ ነው -ፕሬዝዳንት ሽመልስ አብዲሳ - ኢዜአ አማርኛ
የያቤሎ አየር ማረፊያ አገልግሎት መጀመር የዘመናት የልማት ጥያቄ ምላሽ የሰጠ ነው -ፕሬዝዳንት ሽመልስ አብዲሳ
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 25/2017(ኢዜአ)፦ የያቤሎ አየር ማረፊያ አገልግሎት መጀመር የዘመናት የልማት ጥያቄ ምላሽ የሰጠ፤ የህዝቡንም ተጠቃሚነት በተግባር ያረጋገጠ ነው ሲሉ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት ሽመልስ አብዲሳ ገለፁ።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በኦሮሚያ ክልል ቦረና ዞን የያቤሎ አውሮፕላን ማረፊያን አገልግሎት አስጀመሯል።
በዚሁ ወቅት ፕሬዝዳንት ሽመልስ አብዲሳ እንደገለፁት፤ መንግስት የመሰረተ ልማት ዝርጋታን በማፋጠን የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ከምንጊዜውም በላይ በቁርጠኝነት እየሰራ ነው።
ከመሃል ሀገር ርቀው የሚገኙ አካባቢዎችን በመሠረተ ልማት ተጠቃሚ በማድረግ በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ዘርፎች እኩል ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በቦረና አካባቢ የያቤሎ አየር ማረፊያ ተገንብቶ አገልግሎት መጀመሩም ከቦረና አዲስ አበባ የነበረውን ረጅም መንገድ ያሳጠረ መሆኑን ተናግረዋል።
ይህም ለህዝቡ ዘርፈ ብዙ ተጠቃሚነት ጉልህ ሚና ያለው መሆኑን አንስተው፤ አሁን ላለውና ለመጪው ትውልድ ትልቅ የልማት መንገድ የከፈተ መሆኑን ተናግረዋል።
መንግሥት የህዝቡን የመሠረተ ልማት ጥያቄዎች በተግባር ምላሽ እየሰጠ መሆኑንም ጠቁመዋል።
የቦረና ዞን ዋና አስተዳዳሪ አብዱሰላም ዋሪዮ በበኩላቸው፥ የቦረና ህዝብ ባለፉት ስርዓቶች የልማት ጥያቄዎቹ ትኩረት ሳያገኙ መቆየታቸውን አውስተዋል።
ከሀገራዊ ለውጡ ወዲህ ግን በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) አመራር የልማት ትሩፋት ተቋዳሽ ሆኗል ብለዋል።
ለውጡ የህዝቡን የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት ያረጋገጠ መሆኑን ጠቅሰው፥ የያቤሎ አውሮፕላን ማረፊያ ሥራ መጀመሩም የህዝቡን ተጠቃሚነት ከፍ የሚያደርግ ነው ብለዋል።
የትራንስፖርት አገልግሎትን በማቀላጠፍ ትልቅ የመልማት አቅም መሆኑንም ገልጸዋል።
የዞኑ አስተዳደር የአካባቢውን ቆላማነት መሠረት ያደረገ የውሃና የመኖ ዘላቂ ልማት እየተገበረ እንደሚገኝም አንስተዋል።