ቀጥታ፡

የአካል ጉዳተኞችን መብትና ጥቅሞች ለማስከበር የወጡ ህጎች እና አዋጆች በአግባቡ እንዲተገበሩ ጥረት እየተደረገ ነው

አዳማ፤ ነሐሴ 25/2017 (ኢዜአ)፡- የአካል ጉዳተኞችን መብትና ጥቅሞች ለማስከበር የወጡ ህጎች እና አዋጆች በአግባቡ እንዲተገበሩ ጥረት እየተደረገ መሆኑን የአካል ጉዳተኞች ማህበራትና ድርጅቶች ኃላፊዎች ገለጹ።

የኢትዮጵያ የአካል ጉዳተኞች አጠቃላይ ረቂቅ ፖሊሲ መዘጋጀቱም የአካል ጉዳተኞችን መብት ለማስከበር ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ተገልጿል።

ኢዜአ በአካል ጉዳተኞች መብት እና ጥቅም ዙሪያ ከትግራይ፣ ከአፋርና ከአዲስ አበባ የአካል ጉዳተኞች ማህበራትና ድርጅቶች አመራሮች ጋር ቆይታ አድርጓል።

በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የአካል ጉዳተኞች ኀብረት የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ዮሐንስ አርከበ፣ የአካል ጉዳት በተፈጥሮም ሆነ በሰው ሰራሽ ምክንያት የሚከሰት የጋራ ችግር በመሆኑ የአካል ጉዳተኞችን መብት እንደማንኛውም ዜጋ ማክበር ይገባል።


በዚህ ረገድ መንግስት የአካል ጉዳተኞችን መብት ለማስከበርና ሁለንተናዊ ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ የወጡ ህጎችን ከመቀበል አንስቶ ሌሎች የህግ ማዕቀፎችና መመሪያዎች እስከታችኛው መዋቅር በማውረድ ለተግባራዊነቱ ቁርጠኝነቱን አሳይቷል ብለዋል።

ሆኖም የወጡ ህጎችን በአግባቡ ከመተግባር አኳያ ክፍተቶች እንዳሉ ጠቅሰው በተለይ በትምህርት፣ በጤና መሠረተ ልማትና በሌሎችም ዘርፎች የተበታተነ የህግ አተገባበር መኖሩን በክፍተት አንስተዋል።

በቀጣይም እንዚህ ህጎች እና አዋጆች በአግባቡ ተተግበርው የአካል ጉዳተኞች መብትና ጥቅሞች በተሻለ መልኩ እንዲከበሩ ከባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር እየተሰራ ነው።

አዲስ የተዘጋጀው ረቂቅ ፖሊሲም እነዚህ ተግዳራቶች እንዲፈቱ፣ የህግ ማዕቀፎች እንዲጠናከሩና የነበሩ ክፍተቶች እንዲታረሙ ያግዛል ብለዋል።

የአፋር ክልል ጥምረት የአካል ጉዳተኞች ማህበር ፕሬዝዳንት አሊ ሁሴን በበኩላቸው በሁሉም ዘርፎች አካል ጉዳተኞችን ለማካተትና ለማሳተፍ ጥረት እየተደረገ ይገኛል ብለዋል።

በተለይ ለአካል ጉዳተኞች የሚመጥን የመሠረተ ልማት አውታር ግንባታ እንዲኖር እና የአገልግሎት አሰጣጥ ጉድለትን ለማረም ህጎች አና አዋጆች በአግባቡ እንዲተገበሩ ይደረጋል ብለዋል።

አዲሱ የአካል ጉዳተኞች ረቂቅ ፖሊሲም ለአካል ጉዳተኞች መብቶች መከበር እና መጠበቅ ዓይነተኛ መሣሪያ ሆኖ እንደሚያገለግል ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

'ልሳን ለአካል ጉዳተኞች ድርጅት' መስራችና ዋና ዳይሬክተር ኤደን እቋር፤ አካል ጉዳተኞችን የተመለከቱ ተግባራት ይበልጥ ውጤታማ እንዲሆኑ ጉዳዩን በባለቤትነት እና በኃላፊነት መያዝ ይገባል ይላሉ።

አካል ጉዳተኞችን የእኩል ዕድል ተጠቃሚነትና ሁለንተናዊ ተሳትፎ የሚያረጋግጥ የፖሊሲ እርምጃዎች መወሰዳቸውን አድንቀው ይህም የመብት ጥሰትን ከመከላከል ባለፈ በኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና በፖለቲካዊ ዘርፎች ያለውን ተሳትፎና ተጠቃሚነትን ያሳድጋል ሲሉም ገልጸዋል።

በመሆኑም  በመጽደቅ ሂደት ላይ የሚገኘው የአካል ጉዳተኞች ረቂቅ ፖሊሲ ጸድቆ በአፋጣኝ ወደ ሥራ የሚገባበትን ሁኔታ ለማመቻቸት በጋራ መሥራት አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ረቂቅ ፖሊሲ ላይ ግብአት ለማሰባሰብ ያለመ የባለድርሻ አካላት የምክክር መድረክ ባለፉት ሁለት ቀናት በአዳማ ከተማ ተካሂዷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም