ቀጥታ፡

የፌደራል ፖሊስ ለህዳሴ ግድብ ስኬት የህይወት መስዋዕትነት በመክፈል ጭምር ጉልህ አስተዋጽኦ አበርክቷል - ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 25/2017(ኢዜአ)፦ የፌደራል ፖሊስ ከሀገር መከላከያ ሰራዊት ጋር በመሆን የህይወት መስዋዕትነት በመክፈል ጭምር የህዳሴ ግድብ ለስኬት እንዲበቃ ጉልህ አስተዋጽኦ ማበርከቱን የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል ገለጹ፡፡

በሁሉም ኢትዮጵያዊያን ርብርብ የተገነባው ታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ከቀናት በኋላ ለምርቃት ይበቃል።

ግድቡ የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ እድገት ለማፋጠን እና የሀገሪቱን የኢንዱስትሪ ዘርፍ ለማጠናከር ትልቅ አስተዋፅኦ አለው።

በተለያየ መልኩ የግድቡን የግንባታ ሂደት ለማደናቀፍ ሙከራ ቢደረግም በጸጥታ ሀይሉ ቅንጅታዊ ስራ በማምከን ግድቡን ለፍጻሜ ማድረስ ተችሏል።

ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል የፌደራል ፖሊስ የህዳሴ ግድብ መሰረት ከተጣለበት ጊዜ አንስቶ ከሌሎች የጸጥታ ሀይሎች ጋር በመቀናጀት ለውጤት እንዲበቃ ጉልህ አስተዋጸኦ ማድረጉን ተናግረዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ድንቅ አመራር ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከነበረበት ውድቀት ማዳን መቻሉን ገልጸው፤ የህዳሴ ግድብ ዳግማዊ ዓድዋ መሆኑን ገልጸዋል።

የህዳሴ ግድብ እዚህ እስኪደርስ የፌዴራል ፖሊስ አባላት ከገንዘብ በተጨማሪ በህይወት የከፈሉት ውድ መስዋትነት ድርብ ድል መሆኑን አመላክተዋል።

በተጨማሪም ለግድቡ በግብዓትነት የሚያገለግሉ መሳሪያዎችን ከጅቡቲ ድንበር አንስቶ እስከ ግድቡ ድረስ ደህንነቱ በተጠበቀ መንገድ እንዲደርስ መደረጉን ተናግረዋል።

በተከታታይ አመታት ቦንድ በመግዛት አለኝታነቱን ማስመስከሩን ጠቁመው፤ የፌደራል ፖሊስ በሁሉም መንገድ ለውጤት እንዲበቃ ጉልህ አሻራውን ማሳረፉን ገልጸዋል።

በቀጣይም የግድቡን ደህንነት የሚጠብቁ የባህር ላይ እና ዳርቻዎች የጥበቃ አባላትን ማስመረቁን ገልጸው፤ ተመራቂዎች ከሌሎች የጸጥታ ተቋማት ጋር በመቀናጀት እንደሚሰማሩ አመላክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም