ቦረና ብሔራዊ ፓርክ ከ286 በላይ የአዕዋፍ ዝርያዎች መኖሪያ ሲሆን አራቱ በብቸኝነት ይገኙበታል - ኢዜአ አማርኛ
ቦረና ብሔራዊ ፓርክ ከ286 በላይ የአዕዋፍ ዝርያዎች መኖሪያ ሲሆን አራቱ በብቸኝነት ይገኙበታል

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 25/2017 (ኢዜአ)፡- ከ1 ሺህ የሚልቁ የእጽዋት ዝርያዎች መገኛ የሆነው የቦረና ብሔራዊ ፓርክ አቀማመጡ (ተፈጥሮው) ድንቅ መሆኑን የፓርኩ ዋርድ ንጉሴ ዋታ ገልጸዋል።
ከ286 በላይ አዕዋፋት እንደልብ የሚናኙበት መሆኑንና ከእነዚህ ውስጥ አራቱ በቦረና ብሔራዊ ፓርክ ብቻ የሚገኙ ናቸው ሲሉ ለኢዜአ ተናግረዋል።
በተጨማሪም ከ46 በላይ የአጥቢ እንስሣት እና ከ1 ሺህ በላይ የእጽዋት ዝርያዎች መኖሪያ ነው ይላሉ።
በፓርኩ ከአጋር አካላት ጋር በመተባበር በቋሚ እና ጊዜያዊ በማኅበር በማደራጀት ጭምር በተለያዩ ዘርፎች ለበርካታ ወገኖች የሥራ ዕድል መፍጠር መቻሉንም አንስተዋል።
ይህን ለበርካቶች የገቢ ምንጭ የሆነ ፓርክ ሕብረተሰቡ እና መንግሥት በትኩረት እየጠበቁት መሆኑን እና አበረታች ውጤት መገኘቱን ይገልጻሉ።
ለጎብኚዎች ምቹ መሆኑን ጠቁመው፤ ከያቤሎ በአራቱም አቅጣጫዎች የቦረና ብሔራዊ ፓርክን ማግኘት እንደሚቻል ጠቅሰዋል።
አሁን ላይ አጠቃላይ ስፋቱ 6 ሺህ 700 ኪሎ ሜትር ስኩየር መሆኑን አንስተው፤ ቀደም ሲል የእንስሳት መጠለያ እንደነበርና ከሰኔ 2005 ዓ.ም ጀምሮ በተደራጀ አግባብ ብሔራዊ ፓርክ ሆኗል ይላሉ።
በአቀማመጡ ለዕይታ ከመማረክ በተጨማሪ ለአዕዋፋት፣ የተለያዩ የዱር እንስሣት እና በርካታ እጽዋት ዓይነቶች መገኛ የሆነውን ፓርክ በዩኔስኮ ለማስመዝገብ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እየተከናወኑ ነው ብለዋል።
ፓርኩ ሰላማዊ፣ ጽዱ እና ለነዋሪዎች ምቹ መሆኑን ገልጸው፤ ወደ ፓርኩ ለሚመጡ ጎብኚዎች የመጓጓዣ አማራጭ ከመስፋቱ ጋር በተያያዘ በቀጣይ የማረፊያ ሆቴል እና ሎጂ በሥፋት መሠራት እንደሚኖርበት አመላክተዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከዛሬ ጀምሮ ወደ ያቤሎ አውሮፕላን ማረፊያ በሳምንት ሦስት በረራዎችን ለማድረግ የሚያስችለውን ዝግጅት ማጠናቀቁን ማሳወቁ ይታወሳል።
የአየር ትራንስፖርት መጀመሩ የጎብኚዎችን የመጓጓዣ አማራጭ በማስፋት የጎብኚዎች ቁጥር እና በዚያው ልክ የፓርኩና የአካባቢው ማኅበረሰብ ተጠቃሚነት እንደሚያድግ አቶ ንጉሴ ተናግረዋል።