ቀጥታ፡

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያን የመፈጸም አቅም በተግባር ያረጋገጠና መልካም ገጽታዋን ለዓለም ያሳየ ነው

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 24/2017 (ኢዜአ):-ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያን የመፈጸም አቅም በተግባር ያረጋገጠና መልካም ገጽታዋን ለዓለም ያሳየ መሆኑን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ገለጹ። 

ኢትዮጵያዊያን በራሳቸው የእውቀትና የፋይናንስ አቅም የገነቡት ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሊመረቅ ጥቂት ቀናት ብቻ ቀርተውታል።  

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሁሉም ኢትዮጵያዊያን በጋራ የተሳተፉበት እና ህዝቡን አንድ ያደረገ ዳግማዊ ዓድዋ መሆኑን ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ገልጸዋል።

ግድቡ ሁሉም ኢትዮጵያዊያን በጋራ ያሳኩት ትልቅ የልማት ፕሮጀክትና ሁሉንም በጋራ ያሰባሰበ መሆኑን ገልጸዋል።

የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ትምህርት ቤት መምህርት አጋረደች ጀማነህ (ዶ/ር) በሰጡት አስተያየት፤ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ መጠናቀቅ ኢትዮጵያዊያን ነጻነታቸውን እንዳስከበሩ ሁሉ በኢኮኖሚ በኩል አገራቸውን ማልማት ይችላሉ የሚለውን ለሌሎች በተግባር ያስመሰከሩበት ነው ብለዋል። 


 

ጥቁሮች ዓለምን ለመቀየር ብቃት እንዳላቸው ኢትዮጵያ ዳግም ያሳየችበት ትልቅ ስራ መሆኑንም ተናግረዋል። 

ምሁራን የታላቁ ህዳሴ ግድብን የጋራ ተጠቃሚነት የሚያጎሉ ስራዎች በማከናወን የበለጠ እንዲታወቅ መስራት ይጠበቅብናል ብለዋል። 

የሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ትምህርት ቤት መምህር ኃይለጊዮርጊስ ማሞ (ዶ/ር) እንዳሉት፤ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በዓለም ላይ የኢትዮጵያን ገጽታ የሚቀይር ነው።


 

ኢትዮጵያዊያን ካለምንም ልዩነት ለአንድ ዓላማ በጋራ በመተባበር እንደሚችሉ ያሳዩበት መሆኑንም ገልጸው፤ ይህም በቀጣይ ለትላልቅ ስራዎች የሚያነቃቃ እና የህዝቡን አንድነት ያጠናከረ መሆኑን ተናግረዋል።

እንደከዚህ ቀደሙ ሁሉ ምሁራን ከየትኛውም አቅጣጫ በግድቡ ላይ የሚነሳውን አሉታዊ ተጽዕኖ በጋራ የመቀልበስ ስራዎች በተጠናከረ ሁኔታ መስራት አለብን ብለዋል።

የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ትምህርት ቤት መምህር ረዳት ፕሮፌሰር መኩሪያ መካሻ በበኩላቸው፤ የሁሉም ኢትዮጵያዊ አስተዋጽዖ ያረፈበት የዓባይ ግድብ አሁን ለኢትዮጵያ ትልቅ በረከት ሆኗል ብለዋል። 


 

ግድቡ መገንባቱ በርካታ ኢትዮጵያዊያን የኤሌክትሪክ ሃይል ተጠቃሚ እንዲሆኑ ያስችላል፤ ትላልቅ ኢንቨስትመንቶች እንዲሳኩ ያግዛል ብለዋል።

በቀጣይ ህዝብና መንግስት ሌሎች ትላልቅ ፕሮጀክቶችን ለመገንባት እንዲያስቡ ያነቃቃ ትልቅ የመልማት አቅም የፈጠረ መሆኑን ተናግረዋል።

ምሁራን ከዚህ በፊት ግድቡን ከተለያዩ የውጪ ጫናዎች ለመከላከል ከፍተኛ አስተዋጽዖ ሲያበረክቱ መቆየታቸውን ገልጸው፤ አሁን ይህንኑ አጠናክረው መቀጠል አለባቸው ብለዋል።

ግድቡ ከኢትዮጵያም አልፎ የሌሎች አገራትንም የጋራ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ መሆኑን አመልክተው፤ ምሁራን ይህንን በሚያሳይ መልኩ የጀመሩትን ስራ አጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም