በወላይታ ዞን 3 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ካፒታል ያስመዘገቡ 74 ባለሀብቶች ፈቃድ ወስደው ወደ ሥራ ገብተዋል - ኢዜአ አማርኛ
በወላይታ ዞን 3 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ካፒታል ያስመዘገቡ 74 ባለሀብቶች ፈቃድ ወስደው ወደ ሥራ ገብተዋል
ወላይታ ሶዶ ፤ ነሐሴ 24/2017 (ኢዜአ):-በወላይታ ዞን 3 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ካፒታል ያስመዘገቡ 74 ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ ወስደው ወደ ሥራ መግባታቸውን የዞኑ አስተዳደር አስታወቀ።
የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ ረዳት ፕሮፌሰር ሳሙኤል ተሰማ በዞኑ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ሥራዎችን አስመልክተው ዛሬ መግለጫ በሰጡበት ወቅት እንደገለጹት፣ በዞኑ ኢንቨስትመንትን ጨምሮ ኢኮኖሚያዊ እድገትን የሚያፋጥኑና የህዝብን ኑሮ የሚያሻሽሉ የልማት ሥራዎች እየተከናወኑ ነው።
ቀልጣፋ አሰራር ከመዘርጋት በተጨማሪ ዞኑ ለኢንቨስትመንት ያለውን አማራጭ በመጠቀም በርካታ ባለሀብቶች መዋዕለንዋያቸውን በማፍሰስ ወደሥራ መግባታቸውን ገልጸዋል።
በዚህም በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከ3 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ ባለሀብቶች ፈቃድ ወስደው ወደስራ ገብተዋል ብለዋል።
ባለሀብቶቹም በግብርና፣ በአገልግሎትና ኢንዱስትሪ ዘርፍ የተሰማሩ መሆናቸውን ዋና አስተዳዳሪው ጠቁመዋል።
በእነዚህ ዘርፎች ለተሰማሩት ባለሀብቶች 15 ሺህ 300 ሄክታር መሬት መሰጠቱን ጠቁመው፣ ተጨማሪ 58 ፕሮጀክቶች የሥራ ፕሮፓዛል አቅርበው በመጠባበቅ ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በዞኑ ለልማት የወሰዱትን መሬት ሳያለሙ አጥረው ላስቀመጡ 31 ፕሮጀክቶች ማስጠንቀቂያ እንደተሰጠና ሌሎች 10 ፕሮጀክቶች ፈቃዳቸው ተሰርዞ የወሰዱት 1 ሺህ 300 ሄክታር መሬት ወደ መሬት ባንክ እንዲመለስ መደረጉን ተናግረዋል።
ወደ ስራ የገቡት ባለሃብቶች ለ48 ሺህ ሰዎች ቋሚ እና ጊዜያዊ የሥራ ዕድል እንደፈጠሩም ዋና አስተዳዳሪው አያይዘው ገልጸዋል።
በዞኑ የህዝብን የልማት ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ተግባራትም ተጠናክረው መቀጠላቸውን ገልጸው፣ ለዚህም በፌዴራልና በክልል መንግስት ድጋፍ የሚከናወኑ መሰረተ ልማት ዝርጋታዎችንም በማሳያነት ጠቅሰዋል።
የመሰረተ ልማት ሥራዎችን ለማፋጠን በተቀናጀ መንገድ የቅርብ ክትትልና ድጋፍ እየተደረገ መሆኑንም አመልክተዋል።
ለአብነት በፌደራል መንግስት ድጋፍ እየተገነባ ያለው የወይቦ መስኖ ግድብ ፕሮጀክት ተጀምሮ በካሳ ክፍያና ተያያዥ ችግሮች ምክንያት ተስተጓጉሎ እንደነበር አስታውሰው፣ በአሁኑ ወቅት በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ሥራ ለማስገባት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
የክልሉ እና የዞኑ አስተዳደር ከቦታው ለሚነሱ ባለይዞታዎች 110 ሚሊዮን ብር ማዘጋጀቱንም ገልጸዋል።
ግድቡንም በ2018 ዓ.ም በሙሉ አቅም ወደ ስራ ለማስገባት ይሰራል ሲሉም አመልክተዋል።
ሌላኛው በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ልዩ ክትትል በአረካ ከተማ አስተዳደር እየተገነባ የሚገኘው የሱማሜ አየር ማረፊያም ሥራው እየተከናወነ መሆኑን ዋና አስተዳዳሪው ገልጸዋል።
ወቅቱ ክረምት በመሆኑ የካምፕ ግንባታ፣ የውሃ ቁፋሮ፣ የመንገድ ከፈታና መሰል ሥራዎች በመከናወን ላይ መሆናቸውን አመልክተዋል።
በክልሉ መንግስት ድጋፍ በዳሞት ወይዴ ወረዳ የተጀመረው የመስኖ ግንባታ 462 ሚሊዮን ብር ተመድቦለት እየተከናወነ እንደሚገኝም ነው የገለጹት።
በዞኑ በትምህርት፣ በጤና፣ በግብርናና በሌሎችም ዘርፎች የህዝብን ተጠቃሚነት ለማሳደግ የሚከናወኑ የልማት ሥራዎችም ተጠናክረው መቀጠላቸውን ዋና አስተዳዳሪው አረጋግጠዋል።